ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል።

1
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎አምረፍ ሄልዝ አፍሪካ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት የአማራ ክልል የሥራ መሪዎች በተገኙበት ትርጉም ያለው የወጣቶች ተሳትፎ፣ የጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ሕግ ትግበራ እና በወጣቶች ሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
‎በመድረኩ የአማራ ክልል ምክር ቤት ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የክልል ቢሮ ኀላፊዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አጋር አካላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ የተገኙት ‎የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ አምሪፍ ሄልዝ አፍሪካ ግብረ ሰናይ ድርጅት በወጣቶች እና በጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደብረ ብርሃን ከተማ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ሰሜን ጎጃም ዞን እና በባሕር ዳር ከተማ የሚሠራ ነው ብለዋል።
‎በክልላችን ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተስፋፋውን የጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቀረት የተሠራው ሠራ የሚበረታታ እንደኾነም ገልጸዋል። የተሠሩ መልካም ተግባራት ወደ ሌሎች አካባቢዎችም እንዲሰፋ መሠራት አለበት ነው ያሉት።
‎አምረፍ ሄልዝ አፍሪካ ግብረ ሰናይ ድርጅት የአማራ ክልል አሥተባባሪ ደሴ ካሳ ድርጅቱ ባለፉት አራት ዓመታት በክልሉ በብቃት ለወጣት ፕሮጀክት ያከናወናቸውን ተግባራት ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።
‎‎በክልሉ በድርጅቱ በተሠሩ ተግባራት ሕዝብ በሚወከልባቸው ቦታዎች ወጣቶች እንዲሳተፉ መደረጉን እና በጤና ተቋማት ቦርድ ላይ ወጣቶች እንዲሳተፉ መደረጉንም አንስተዋል።
‎በየአካባቢው ያሉ የማኅበረሰብ አጀረጃጀቶች፣ ዕድሮች እና የሃይማኖት ተቋማት በጋራ በመተባበር “ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን” ገልጸዋል።
‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይዎት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበዞኑ ውጤት ማምጣት የቻሉ ሥራዎች ተሠርተዋል።
Next articleበከተማ አሥተዳደሩ እመርታዊ ውጤት ማምጣት የቻሉ ሥራዎች ተሠርተዋል።