
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አንተ ምድር ካየቻቸው አፍላጋት ሁሉ ትልቃለህ፤ አንተ ታሪክ ከሚያውቃቸው ወንዞች ሁሉ ትገዝፋለህ፤ አንተ በቅዱስ መጽሐፍ ስማቸው ከሰፈሩ አፍላጋት መካከል አንደኛው ነህ።
አንተ ከተመረጡት መካከል ተመርጠሃል፤ ከተለዩት ተለይተሃል፤ ከገዘፉት ሁሉ ገዝፈሃል፤ አንተ ታሪክ አሳሾች ምንጭህን ያገኙ ዘንድ ተከትለውሃል፤ ባገኙህም ጊዜ አብዝተው ተደስተውብሃል።
እረኞች ዋሽንታቸውን እያንቆረቆሩ አዜመውልሃል፤ ታላላቆቹ ተቀኝተውልሃል፤ ሊቃውንቱ አደራ ጥለውብሃል፤ ምሥጢር አስቀመጡብሃል፤ ጠቢባን ጥበብን ጨለፈውብሃል፤ ሥልጣኔን ቀድተውብሃል፤ ፍቅር እና አንድነትን አትመውብሃል።
የከፋቸው ተጠልለውብሃል፤ ነጋዴዎች የደከሙ ፈረሶቻቸውን፣ የተጠሙ በቅሎዎቻቸውን እና የዛሉ ግመሎቻቸውን አጠጥተውብሃል፣ እነርሱም ከጥም ረክተውብሃል፤ ከእድፍም ነጽተውብሃል፤ የዛሉት በርትተውብሃል፤ የደከሙት ነቅተውብሃል፤ ግዮን።
ምድር ከአንተ የረዘመ አፍላግ አልተመለከተችም። ከአንተ የላቀ ታላቅም አላየችም። በአንተ እንዳገኘችው ሥልጣኔ በሌላ አላገኘችም፤ ከአንተ እንደቀዳችው ጥበብ ከሌላ አልቀዳችም፤ ከአንተ እንደ ወሰደችው ፍልስፍና ከሌላ አልወሰደችም። አንተ ለፈለቅህባት ሀገር ብቻ ሳይኾን ለዓለምም ሲሳይ ነህ፤ ለሁሉም ብርቅ እና የጥበብ ምንጭ ነህ።
ኢትዮጵያውያን ሥልጣኔን ሠርተውብሃል፤ ጥበብን አትመውብሃል፤ ታላቅነትን አሳይተውብሃል፤ ጥንታዊነትን ለዓለም ነግረውብሃል፤
ግዮን ወንዝ ብቻ አይደለም አእዋፋት የሚጠጡበት፤ ግዮን ወንዝ ብቻ አይደለም የአደፉ ልብሶች የሚነጡበት፤ የተጠሙ የሚረኩበት፤ ግዮን ወንዝ ብቻ አይደለም ውኃ የሚፈስስበት፤ እርሱ ኢትዮጵያውያን ታሪክ የሚጽፉበት የማይነጥፍ ቀለም ነው፤ እርሱ ጥበብ የሚያትሙበት ረቂቅ ማህተም ነው፤ እርሱ ቀደምትነትን የሚያሳዩበት ሕያው ምስክር ነው፤ እርሱ ምስጢር የሚተውበት ታማኝ ነው፤ እርሱ የሀገሬው እረኞች እና ገበሬዎች ብሶታቸውን የሚያካፍሉት የክፉ ቀን ጓደኛ ነው፤ እርሱ ታሪክ የሚነበብት ብራና ነው፤ እርሱ የተቀደሰ አፍላግ ነው።
ኢትዮጵያውያን ከጥንት እስከ ዛሬ ከግዮን ጋር ጥብቅ ትስስር አላቸው። ያዘኑ በዳሩ ተቀምጠው ሀዘናቸውን በዜማ ይነግሩታል። የናፈቁ በአሻገር ኾነው ናፍቆታቸውን ይወጡበታል። መንጻት የፈለጉም ከውኃው ጨለፍው ይነጹበታል። ዘርን የሚዘሩም በዳሩ ዘር ዘርተው ፍሬ ይቀምሱበታል።
በኢትዮጵያ ብቻ በምትታወቀው፣ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ምሥጢር በሚያመሰጥሩባት በወርኃ ጳጉሜን
ደግሞ በግዮን ላይ ታላቅ ነገር ይፈጽማሉ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች ወርኃ ጳጉሜን ስትደርስ ጠበል ይጠመቃሉ። አምላክ ከሐጥያት፣ ከደዌ እንዲያነጻቸው አሮጌውን ዓመት በሰላም እንዲያሳልፍላቸው፣ አዲሱን ዓመት በሰላም እንዲያቀዳጃቸው ይማጸኑታል።
ወርኃ ጳጉሜን በጾምም ያሳልፏታል። ሕጻናት ጳጉሜን ስትደርስ አብዝቶ ደስ ይላቸዋል። ሌሊቱ ሊነጋጋ ሲል በየመንደሩ እየተጠራሩ፣ ውኃውን ወፍ ሳይቀምሰው ወደ ወንዝ ወርደው ይጠመቃሉ።
ከወርኃ ጳጉሜን ሦስተኛዋ ቀን ደግሞ ደምቃ ትከብራለች። በጳጉሜን ሦስት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል ይከበራል። ምዕምናን ሩፋኤል በደረሰ ጊዜ ደስ ይሰኛሉ። በማለዳ እየወጡ ወደ ወንዝ እየወረዱ ይጠመቃሉ። ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄዱም ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይፈጽማሉ። በዚህ ቀን የሚዘንብ ዝናብ ፀበል እንደሆነ ይታመናል። ልጆች በሩፋኤል ቀን የሚዘንበው ዝናብ እንዲያልፋቸው አይሹም። ዝናቡ የበረከት ዝናብ ነውና። ዝናብ ሲመጣ ልብሳቸውን እያወለቁ ይመታሉ።
በጋራ ዝናብ እየተመቱ ደስታን ያደርጋሉ። በሩፋኤል ቀን በኅብረት ያዜማሉ፤ ይዘምራሉ። ሩፋኤል ከሽንብራው ጎታ (ጎተራ) ክተተኝ ይላሉ።
” ዝናቡ ቸሬ
አንዝበው ዛሬ” እያሉ ዝናብ እንዲመጣና ዝናቡ እንዲመታቸው ይለምናሉ። ለወትሮው ዝናብ ሲመጣ መጠለያ የሚያደርጉት እረኞች እና ሕጻናት የሩፋኤል ቀን ግን ዝናብ ሲመጣ በደስታ ይመታሉ። ልብሳቸውን አውልቀው በደስታ ይፍነከነካሉ።
በዚህ ቀን በታላቁ ወንዝ በግዮን ክብረ በዓሉ ይደምቃል። በደጀን እና በጎሃ ጽዮን መካከል በዓባይ ወንዝ ዳር የሩፋኤል ክብረ በዓል ደምቆ ይከበራል። ዓመቱን ሙሉ የተነፋፈቁ የአማራ እና የኦሮሞ ደጋጎች የሩፋኤል ቀን በዓባይ ወንዝ በአንድነት ይገናኛሉ።
በአንድነት ይጠመቃሉ። በአንድነት ይነጻሉ። ስለ አከራረማቸው፣ ስለ አዝመራው፣ ስለ ልጆቻቸው፣ ስለ ከብቶቻቸው፣ ስለ ሀገራቸው ይጠያየቃሉ። በአንድነት ማዕድ ይቆርሳሉ። በአንድ ጽዋ ከሚጠጣው ይቀምሳሉ። በዓባይ ወንዝ በሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን አጸድ ሥር ስለ ሀገራቸው ሰላም፣ አንድነት እና ፍቅር ይማጸናሉ፤ ይጸልያሉ።
በዓባይ ወንዝ አንድነት ይሰበካል። ፍቅር ከፍ ይላል፣ ኢትዮጵያዊነት ይጸናል እንጂ መለያየት፣ ጠብና ጥላቻ ቦታ የላቸውም። ስለሚያለያዩ የፖለቲካ ስብከቶች፣ ጥላቻን ስለሚዘሩ አንደበቶች አይሰሙም። እነርሱ እንደቀደውም ሁሉ አንድነትንና የጸናች ኢትዮጵያዊነትን ያጸናሉ እንጂ።
በወርኃ ጳጉሜን በሦስተኛው ቀን ዓመታዊ ክብረ በዓሉ የሚከበረው ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወርኃ ጳጉሜን የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ ይህም ጳጉሜን ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት፣ ከክረምት ወቅት ወደ ጸደይ መሸጋገሪያ እንደኾነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ፣ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ፣ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ናት ይላሉ አበው።
ጳጉሜን የክረምቱ ማብቂያ እንደኾነች ሁሉ ምጽአትም በመጨረሻው ዘመን መከራ የሚበዛበት የዚህ ዓለም ማብቂያ ናት፡፡ ወርኃ ጳጉሜን አዲሱን ዓመት ለመቀበል የዝግጅት ጊዜ እንደኾነች ሁሉ ምጽአትም ጻድቃን መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ተዘጋጅተው “ኑ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” የሚባሉባት ናት፡፡ ለዚህም ነው ምዕመናን በጾምና በጸሎት የሚበረቱባት።
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ በዓል በጳጉሜን ሦስት ሰማያት የሚከፈቱበት (ርኅዎተ ሰማይ) ናትም ይባላል። በዚህች በተከበረችው ዕለት ምዕመናን ጸሎታቸው ያርግላቸው ዘንድ ተግተው ይጸልያሉ፡፡
ርኅወተ ሰማይ የስሙ ትርጉም የሰማይ መከፈት ማለት ነው ይባላል። ክርስቲያኖች ሁሉ ጸሎት፣ ልመናቸው ምልጃቸው የሚያርግበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት የምዕመናንን ልመና መሥዋዕቱን የሚያሳርጉበት እና የአምላካቸውን ምኅረት፣ ቸርነት ለሰው ልጆች የሚያወርዱበት ዕለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ውኆች እንደሚባረኩ በጽኑ እምነት በማመን ምዕመናን ወደ ወንዞች በመሄድና በሚዘንበው ዝናብ ይጠመቃሉ፡፡
በጳጉሜን ወደ ግዮን ወንዝ እየወረዱ እየተጠመቁ ይነጻሉ። ወደ ቤታቸውም ሲመለሱ ከወንዙ እየቀዱ ጸበል ይወስዳሉ። ታላቁ ወንዝ በረከት የሚያስገኝ ነውና ለበረከት የሚኾን ሁሉ ወደ ቤታቸው ይወስዳሉ።
በጳጉሜን ሦስት በሩፋኤል ቀን “ከወደ ጎጃም የሄዱት ድልድዩን ተሻግረው በሸዋ በኩል፣ ከሸዋ የመጡት ደግሞ ድልድዩን ተሻግረው በጎጃም በኩል ወደ ወንዙ እየገቡ ይጠመቃሉ። እንዲህም የሚያደርጉበት ምክንያት አንድም ከዓመት ዓመት እንኳን አደረሳችሁ ለመባባል፣ ለመጠያየቅ፣ ሁለትም ዓባይን ተሻግሮ መጠመቅ ሊኖር የሚችለውን ሕመም አሻግሮ ለመጣል ነው” ይባላል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዓባይ ማዶና ማዶ የቅዱስ ሩፋኤልን እና የአቡነ ዘርዓብሩክን አብያተ ክርስቲያናት አንጻለች። በሩፋኤል ቀንም ከሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ታቦታቱ ወጥተው በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ድልድይ ላይ ተገናኝተው ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ይፈጸማል። ሊቃውንት ይዘምራሉ። ምዕምናን እልል ይላሉ። ታቦታቱ ወንዙን ይባርካሉ፣ ይቀድሳሉ።
ይህ በዓል በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚያከብሩት፣ የቱሪዝም ሀብት ነው። በዓሉ ሕዝብን ከሕዝብ በማገናኘት አንድነት የሚፈጥር፣ መልካም ግንኙነትን የሚያጠናክር ነው። የጋራ በዓል ነውና በጋራና በአንድነት ይከበራል።
ታላቁ አፍላግ ያስተሳስራል፣ በአንድነት ያቆማል፣ በፍቅር ያገናኛል። ታላቁ ወንዝ ግዮን ለኃይሉ ገባሮችን እንደሚያገናኘው ሁሉ ኢትዮጵያውያንንም በአንድነት ያገናኛል። የአንድነት ኃይልን ይጨምራል።
በዓሉ ሲፈጸም ከዓመት ዓመት እንዲያደርሳቸው፣ በሰላምና በፍቅር እንዲጠብቃቸው ለታቦታቱ ስለት ሰጥተው ይለያያሉ። ዓመት ደርሶ ዳግም እንዲገናኙ መልካሙን ሁሉ ተመኝተው በፍቅር ይለያያሉ። ዓመት ደርሶ እንደሚገናኙም ያምናሉ። ያ ይፈጸም ዘንድ አብዝተው ይጸልያሉ።
ዘጋቢ:- በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን