
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከጎንደር ከተማ የተወጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች በኦሮሚያ ክልል አምቦ እና ወንጪ ታሪካዊ ሥፍራዎችን እና የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝት መርሐ ግብሩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ ኅብረሰተብ ክፍል ተወካዮች ተገኝተዋል።
ተሳታፊዎቹ በጉብኝታቸው በአምቦ ከተማ የኮሪደር ልማት፣ ታሪካዊቷን የደብረ ገነት ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም እንዲሁም የወንጪ እና ደንዲ ኤኮ ቱሪዝምን ተመልክተዋል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በዚሁ ወቅት በአምቦ እና ወንጪ አካባቢ ሲደርሱ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
በወንጪ በምትገኘው ታሪካዊቷ የቅዱስ ቂርቆስ ገዳም በጎንደር እና ወንጪ መካከል ከ400 ዓመታት በፊት የተከናወነ አስደናቂ ተግባር ማየታችን አስደንቆናል ብለዋል።
አፄ ፋሲለደስ ለወንጪ ቂርቆስ የሰጡት እና ስማቸው የተጻፈበትን ደወል በገዳሟ በመመልከታቸው መደነቃቸውንም ገልጸው። የኢትዮጵያውያን የትስስር ገመድ ከጥንተ ታሪክ እንደሚመነጭ ማሳያ መኾኑን አውስተዋል፡፡
ከአምቦ አካባቢ በተወሰደ ኖራ ዕድሳት የተደረገለት የጎንደር አብያተ መንግሥት ታሪካዊ ቅርስም የጎንደር እና ወንጪን ታሪካዊ ትስስር የሚያረጋግጥ እንደኾነ አስረድተዋል።
የጎንደር ቅርሶች ዕድሳት እና የወንጪ ቂርቆስ ገዳም ቅርሶች ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ አንድነት የምትሰራ ሀገር መኾኗን እንደሚያሳዩ ነው አቶ ቻላቸው ያወሱት።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ሕዝብ በማስተባበር የታሪካዊቷን ገዳም የሙዝዬም እና ተያያዥ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚደግፍ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያውያን የትስስር ገመድ የማይበጠስ እና ከጥንተ ታሪክ እንደሚመነጭ የቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ሕያው ምስክር መኾኗ በጉብኝት መርሐ ግብሩ ወቅት ተጠቅሷል፡፡
ጉብኝቱ ርቀት ያልገደበው ከጥንት ታሪክ የሚመነጭ የሕዝብ ለሕዝብ ትሥሥርን ለማስቀጠል ትምህርት ሰጪ መኾኑም ተመላክቷል፡፡
የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አጫሉ ገመቹ በበኩላቸው የጎንደር ከተማ እንግዶች ባደረጉት ጉብኝት መደሰታቸውን ገልጸዋል። ጉብኝቱ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ምንጭ የሚቀዳ አስተሳሳሪ ገመድ እንዳለን እንድንገነዘብ ያደረገ ነው ብለዋል።
በተፈጥሮ ጸጋ የበለጸገው የገበታ ለሀገር የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ አድርጓል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከጎንደር ከተማ የተወጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች የቅድመ አያቶቻቸውን ታሪክ የሚያስቀጥል ድጋፍ ለማድረግ ለሙዝየሙ መልሶ ግንባታ ለገቡት ቃል ምስጋና አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!