
አዲስ አበባ: ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አፍሪካ አሁን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተደመረ መፍትሔ እየወሰደች ነው ብለዋል።
በግል ብቻ የሚወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጡ በመገንዘብ ወደ ተደራጀ ሁነት አሕጉሪቱ እየመጣች እንደኾነም ፕሬዝዳንቱ አስገንዝበዋል።
ባለፈው ዓመት በኬንያ እና በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ የተካሄዱ እና እየተካሄዱ ያሉ ጉባኤዎችን እንደማሳያም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በጀት መድባ ለዚህ ሁነት መሠባሠብ ቆራጥነት ስላሳየች ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አመሥግነዋል።
ይህ ሁነት ተራ ሥብሠባ ሳይኾን በቀጣይ የጋራ መፍትሄ የሚወሰድበት እና አቅጣጫ የሚቀመጥበት ስለመኾኑም ነው ያብራሩት።
ዛሬ የሚካሄዱ ሥራዎች የሚነገሩ ብቻ ሳይኾን በቀጣይ ተጠያቂነት የሚያስከትሉ መኾን ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የሚሠሩ ሥራዎች በሰው ልጅ ላይ መፍትሔ እንዲያመጡ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል። “ካልኾነ ግን ኀላፊነት የምንወስድበት ሊኾን ይገባል” ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ነች ያሉት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በአዲስ አበባ የሚደረገው ውሳኔ ሁሉ ለሰው ልጅ የሚጠቅም መኾን ይገባዋል ብለዋል።
ለሰብዓዊነት መሥራትም አስገዳጅ መኾኑን ፕሬዝዳንቱ አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን