በአንድ ጀንበር ከመኖሪያ ቤትነት ወደ ሆስፒታልነት፡፡

220

ከ17ቱ የቤተሰብ አባላት 11 የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/2012 ዓ.ም (አብመድ) 17 የቤተሰብ አባላት በአንድ ጣሪያ ሥር ሕይወትን በተለመደው መልክ ይመራሉ፡፡ ምንም እንኳን የዚህ ታሪክ መቼት በህንድ ቢሆንም ነገ የኢትዮጵያውያን ዕጣ ፋንታ ላለመሆኑ ዋስትና የለምና ትምህርት እንዲሆን ልንነግራችሁ ወደድን፡፡ ሙኩል ጋርግ የ57 ዓመት አጎቱ ሚያዝያ 16/2012 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰማቸው የመጣው ትኩሳት ለቤተሰቡ ስጋት አልነበረም፡፡ በ48 ሰዓታት ውስጥ ከ17ቱ ሁለት ተጨማሪ የቤተሰብ አባላት ተመሳሳይ ሕመም ይስተዋልባቸው ጀመር፤ አሁንም ከአራት ወራት ጨቅላ እስከ 90 ዓመታት የዕድሜ ባለፀጋ አንድ ጣሪያ ሥር ያስጠለለው ቤት እውነታውን መቀበል ከብዶታል፡፡

ከሚጠበቁት የኮሮናቫይረስ ዋና ዋና ምልክቶች ተከታታይ ሳል እና ትኩሳት በታማሚዎቹ ላይ ቢስተዋልም እነጋርግ ግን ‘‘ጉንፋን ይሆናል እንጂ ኮሮና ነው’’ ብለው ማሰብ የፈለጉ አይመስሉም፡፡ ከዚህ ቀደም አምስትና ስድስት የቤተሰቡ አባላት በተመሳሳይ በጉንፋን ይጠቁ ስለነበር አሁንም ኮሮናቫይረስ ይሆናል ብለው አልተሸበሩም፡፡ ነገር ግን በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ተጨማሪ አምስት የቤተሰቡ አባላት የሚያሳዩት የሕመም ስሜት ቤተሰቡ ውስጥ አንዳች የስጋት ድባብ ፈጠረ፡፡

ነገሮች እንደተጠበቁት ቀላል አልሆኑም፡፡ በአጎት ተጀምሮ ከቤተሰቡ አባላት አስሩ የተሰማቸው የሕመም ስሜት ከተራ ጉንፋንነት አልፎ ኮሮና መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ አክስት መተንፈስ እስከመቸገር ደርሰው ወደ ሆስፒታል ተወሰዱ፡፡ ህንድ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል በጣለችው የእንቅስቃሴ ዕገዳ ምክንያት በአንድ ጣሪያ ስር ሆነው የተለመደ ሕይወትን ከሚመሩት 17 የቤተሰብ አባላት አስራ አንዱ የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው፡፡ በዚህ መልኩ በአንድ ጀንበር ቤቱ ወደ ሆስፒታልነት ተቀየረ፡፡

የጋርግ አጎት ገበያ አትክልት ተራ ወይም ግሮሰሪ በወጡበት ወቅት ለቫይረሱ ሳይጋለጡ እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡ አነጋጋሪው ጉዳይ ግን በተመሳሳይ መልኩ ከፍተኛ ቁጥር የቤተሰብ አባላት በአንድ ጣሪያ ስር መኖር አዲስ ባልሆነባት ህንድ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በምን አልፎ ስኬታማ ይሆናል? የሚለው ነው፡፡ ለአብነት የነጋርግን ቤተሰብ ብንጠቅስ 17 ቤተሰብ የጋራ መጸዳጃ ቤት፣ ማዕድ ቤትና በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ እስከ ሦስት መኝታዎችን ያቀፈ ነው፡፡ እናም በእንደዚህ ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ ጥንቃቄ የበለጠ ፈታኝ ይሆናል፡፡ የእነጋርግ ቤተሰብ ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር በስልክ እና በስካይፒ ለረጅም ሰዓታት እየተነጋገሩ እየተረዳዱ ነው፡፡

ምንም እንኳን በቫይረሱ ከተያዙት ስድስቱ የልብ፣ የስኳር እና ግፊት ሕመም ቢኖርባቸውም በመጨረሻም ቤተሰቡ እየተረዳዳ ችግሩን ማለፍ ችሏል፡፡ የቤተሰብ ጠቃሚነት ለዚህ ወቅት ነውም ተብሎለታል፡፡

ከመጋቢት 16/2020 ዓ.ም አንስቶ ዜጎቿ በቤት እንዲቆዩ ዕገዳ የጣለችው ህንድ በተወሰነ ደረጃ እንቅስቃሴ የፈቀደችው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን 40 በመቶ የሚሆኑት ህንዳውያን ሕይወትን የሚገፉት በተጨናነቀ ሁኔታ በአንድ ጣሪያ ስር ከሦስት እና አራት በላይ የቤተሰብ አባላት ሆነው ነው፡፡ ጥናቶች የሚያመላክቱትም በህንድ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከቀሪው ዓለም በተለየ መልኩ በስፋት የሚስተዋለው በቤተሰብ አባላት ውስጥ መሆኑን ነው፡፡ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት የእንቅስቃሴ ዕገዳው በተጣለበት ወቅት አንድ የቤተሰቡ አባል በቫይረሱ ከተያዘ ቀሪው ተጠቂ መሆናቸውን ነው፡፡

ይህ ለኢትዮጵያውያን የሚያስተምረው አንድ ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከቡና እስከ ማኅበር፣ ከጸሎት እስከ ዱአ፣ ከሐዘን እስከ ደስታ በተሳሰረ መስተጋብር ውስጥ ያሳልፋሉ፡፡ ይህ በቤት፣ በጎረቤት እና በመንደር ውስጥ አሁንም ያልቆመ ማኅበራዊ መስተጋብር ነው፡፡ የአንድ ግለሰብ በቫይረሱ መያዝ የቤተሰብ አባላት መጎዳት፤ የቤተሰብ ጉዳት የሰፈር ከዚያም የማኅበረሰብ እያለ ትናንት ካየናቸው ሀገራት ያልከፋ ጉዳት ላለመፈጠሩ እርግጠኞች አይደለንም፡፡

ጉዳዩን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ማገር በሆነው የአርሶ አደሩ ቀየ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት አናሳ ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የግንዛቤ ደረጃም “የከተማ በሽታ ነው” ከሚል ያልዘለለ በመሆኑ ተጨማሪ ግንዛቤ እና ተደማሪ ጥረትን ይጠይቃል፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ
በታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየእምቦጭ አረምን በዘላቂነት ለማስወገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተቀናጀ አሠራር እንደሚያስፈልግ የዩኒቨርሲቲዎች የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡
Next articleየሱዳን መንግሥት ከታጣቂ ኃይሎች ጋር የሰላም ስምምነት ሊፈራረም ነው፡፡