“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ አቅም ማሳያ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

5
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ጳጉሜን 3 “እመርታ ለዘላቂ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት እያከበረ ይገኛል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች በተሠጠው ትኩረት ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አንዱ መኾኑንም አንስተዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ቁጭት የታየበት፤ የይቻላል መንፈስ የተረጋገጠበት፤ የውጭ ተጽዕኖን ሰብሮ የወጣ እና “የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ አቅም ያሳየ የድል ፍኖት መኾኑን ነው” የተናገሩት። ሀገሪቱ በቀጣናው ካላት ተሰሚነት አንጻር በብሪክስ አባልነት አድትመረጥም አድርጓታል ነው ያሉት።
አሁን ላይም ኢትዮጵያ ካላት ታሪክ እና የሕዝብ ቁጥር አኳያ የባሕር በር ለማግኘት እየሠራች መኾኑንም ገልጸዋል።
ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ነው የተናገሩት ዶክተር ሙሉነሽ። ለማዕድን ዘርፉም በተሠጠው ትኩረት እንደ ለሚ ሲሚንቶ እና የመሳሰሉ ፋብሪካዎችን ማቋቋም ተችሏልም ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት በየዓመቱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
በክልሉ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ደግሞ የ25 ዓመታት አሻጋሪ ዕቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል። ዕቅዱ እውን እንዲኾን የአሁኑ ትውልድ ታሪካዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
አምራች ትውልድ ለመፍጠር አሁን ላይ የትምህርት ዘርፉ ያጋጠመውን ሥብራት መጠገን ላይ ሁሉም ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየእመርታ ቀን በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ኹነቶች እየተከበረ ነው።
Next article“ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት መፍትሔ ካበረከተቻቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ተጠቃሽ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)