በሀገር ላይ እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል።

2
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎በሀገር አቀፍ ደረጃ ጳጉሜን 3 ’’የዕምርታ ቀን’’ በሚል እየታሰበ ነው፡፡ በዚህ ዕለት በክልሉ በትምህርት ዘርፍ ዕምርታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ጉዳዮች የሚታሰቡበት ነው።
ትምህርት ባሕል እና እሴትን ለመጠበቅ እና ለማኅበረሰብ ዕድገት መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች በርካታ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው መቆየታቸው ይታወቃል።
‎የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ተማሪዎች እንዲማሩ ሁሉም የድርሻውን ቢያበረክት ውጤቱ መልካም ይኾናል።
በ2018 የትምህርት ዘመን በትምህርት ላይ ዕምርታዊ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልጆችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ይጠበቃል፤ እያደረጉም ይገኛሉ፡፡
👉 የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በትምህርት ዙሪያ ምን እየሠሩ ይኾን?
‎የአማራ ክልል የሽምግልና መማክርት ጉባኤ ሠብሣቢ መሪጌታ ብሩህ ዘላለም የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ትምህርት እንዲጀመር ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
‎ሁሉም የሀገር ሽማግሌዎች ቢቻል ሰላምን ለማምጣት ካልኾነ ደግሞ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ትምህርት እንዲሰጥ መሥራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ምንም ቢኾን ትምህርት መቋረጥ የለበትም ብለዋል።
‎ማንኛውም አካል ትውልድ እንዲማር ትምህርትን መፍቀድ አለበት፤ ለሁለት ዓመት ትምህርት በመቋረጡ ትውልድ ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ በመኾኑ ትምህርት መጀመር አለበት ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሀገር ሽማግሌዎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
‎በገጠሩ አካባቢ ትምህርት በመዘጋቱ ያለዕድሜያቸው ወደ ትዳር የገቡ ሴቶች በርካታ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ሴቶች ቀጣይ ትምህርት ቢጀመር እንኳን ልጅ በመውለዳቸው ትምህርታቸውን ለመቀጠል የሚቸገሩት ቁጥራቸው ብዙ ነው ብለዋል፡፡
‎ሠብሣቢው “የትምህርት መቋረጥ ሥራ አጥነትን ያባብሳል፤ ትውልድንም ለሥነ ምግባር ጉድለት ይዳርጋል” ነው ያሉት፡፡ የመማክርት ጉባኤው በዞኖች ያሉ አባል የሀገር ሽማግሌዎችን በመጠቀም ትምህርት እንዲቀጥል እንሠራለን ነው ያሉት፡፡
“ካልተማሩ አያውቁ፤ ካላወቁ አይጸድቁ” የሚለውን የማኅበረሰቡ ብሂል መሠረት በማድረግ የሰውን ልጅ ሰው የሚያሰኘው ዕውቀቱ እና ግንዛቤው መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
‎ማኅበረሰቡ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በራሱ አቅም ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ልጆቹ እንዲማሩ ማድረግ አለበት ነው ያሉት፡፡
‎የመማክርት ጉባኤው ምክትል ሠብሣቢ ይመር ሰይድ ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ እና የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ሁሉም የሀገር ሽማግሌዎች በየአካባቢያችን ከገጠር እስከ ከተማ መሥራት አለብን ብለዋል።
‎ትምህርት እንዲዘጋ ያደረጉ አካላት የማኅበረሰቡ ክፍሎች በመኾናቸው ከቤተሰቦቻቸው እና ከእነሱም ጋር በመነጋገር ትምህርት መጀመር አለበት ነው ያሉት። ትምህርት በመቅረቱ ክልሉ በዕውቀት ወደ ኋላ እየቀረ እና እየተጎዳ ነው ብለዋል።
ከረፈደም ቢኾን የመንግሥት አካል፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ኅብረተሰቡ እና ሁሉም በመረባረብ መመካከር እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ልጆቻችን እንዲማሩ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።
የሀገር ሽማግሌ መማክርት ጉባኤው አባል አለቃ ጥላዬ አየነው በተለይም በገጠሩ የክልሉ አካባቢዎች ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ሰላም ወደኾነው ከተማ በመሄድ የተማሩ አሉ፤ ይህ ደግሞ ወላጆችን ለተጨማሪ ወጭ እንደዳረጋቸው አንስተዋል።
አቅም ያልፈቀደለት ትምህርት አቋርጦ መቆየቱንም ነው የገለጹት። ይህንን በመገንዘብ ማንኛውም አካል ልጆች እንዲማሩ፣ የወላጆች ድካም እንዲቀንስ እና ሀገር እና ሕዝብ በዕውቀት እንዲመራ መፍቀድ ይገባል ሲሉ መክረዋል።
‎እንደ ሀገር ሽማግሉዎች እና የሃይማኖት አባቶች ሁሉ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍልም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት በ2018 ዓ.ም ትምህርት ቤቶች የተዘጉት ተከፍተው ቤት የተቀመጡ እና ከቀያቸው የወጡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው በመመለስ በትምህርቱ ዘርፍ ዕምርታዊ ለውጥ ለማምጣት ርብርብ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡
‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየተሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መሠረታዊ እና ችግር ፈች ናቸው።
Next articleየእመርታ ቀን በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ኹነቶች እየተከበረ ነው።