የተሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መሠረታዊ እና ችግር ፈች ናቸው።

1
ደባርቅ: ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎የማኅበረሰቡን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እና ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሢሠራ መቆየቱን የሰሜን ጎንደር ዞን የከተማ እና የመሠረተ ልማት መምሪያ ገልጿል።
‎የሰሜን ጎንደር ዞን የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ይሁኔ ያዜ በ2017 በጀት ዓመት ከ82 በላይ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ሲያስፈጽሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የመንገድ፣ የመብራት፣ የትምህርት ቤት እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች መከናዎናቸውንም ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ የልማቱ አጋዥ በመኾን በሃሳብ፣ በጉልበት፣ በዓይነት እና በገንዘብ የልማት ሥራዎችን ሲደግፍ መቆየቱንም አንስተዋል።
ማኅበረሰቡ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት በተጨባጭ የልማት አጋርነቱን ማሳየቱንም ገልጸዋል። በተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ከ5ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አብራርተዋል።
‎የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚዎችም የመሠረተ ልማት ሥራዎች ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተጨማሪ አቅም እንደኾኑ ተናግረዋል።
የወጣቶችን የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ዘርፉን ማሳደግ እና ማጎልበት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የባርቅ ከተማ አሥተዳደር የከተማ እና መሠረተ ልማት ጽፈት ቤት ኀላፊ ቢራራ ማሞ ከማኅበረሰቡ ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠር ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ልየታ እና ክንውን መካሄዱንም አብራርተዋል።
‎ማኅበረሰቡ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የልማት ሥራዎችን መደገፉንም አብራርተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ ለተከናዎኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉንም ገልጸዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎችም የተሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መሠረታዊ እና ችግር ፈች ናቸው ብለዋል።
‎የመሠረተ ልማት ሥራዎችን የጋራ አቋም ወስደው በተለያዩ ጉዳዮች ሲደግፉ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።
‎በቀጣይም የልማት ሥራዎችን በመደገፍ እና በመቆጣጠር ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“ኢትዮጵያ በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት በርካታ እመርታዊ ለውጦችን አስመዝግባለች” የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
Next articleበሀገር ላይ እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል።