የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የግብጽ ደጋፊዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ ላሳዩት ያልተገባ ባሕሪ እርምት እንዲወስድ ለፊፋ ጥያቄ አቀረበ።

16
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የግብጽ እግር ኳስ ማኅበርን እና ደጋፊዎቹን በመቃወም ለዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ፊፋ) ኦፊሴላዊ አቤቱታ አቅርቧል።
አቤቱታው የቀረበው ከሰሞኑ በተደረገው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ወቅት የተፈጠረውን ያልተገባ ባሕሪ መሠረት አድርጎ ነው።
ፌዴሬሽኑ ባወጣው መግለጫ የግብጽ ደጋፊዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር በፉጨት፣ በጩኸት እና በሌሎችም ድምፆች በማቋረጥ የፊፋን የሥነ ምግባር ደንብ እንደጣሱ ገልጿል።
በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ “የአንድን ሀገር ብሔራዊ መዝሙር ማክበር የክብር እና የጋራ መከባበር መሠረት ነው” ሲል አፅንኦት ሰጥቷል።
በሌላ በኩል በፊፋ ሕግ የማይፈቀድ ተንቀሳቃሽ መብራት ይዞ በመግባት ግብ ጠባቂው ላይ እና አጥቂ ተጫዋቾቹ ላይ አይናቸው ላይ በማብራት የመረበሽ እና በትክክል እንዳይጫዎቱ የማድረግ ሥራ ሠርተዋል ብሏል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋን ቢዎስዳቸው ያላቸውን ርምጃዎች ጠቅሶ እርምት እንዲወስድ ጠይቋል።
በዚህም መሠረት፦
በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ወቅት ለተፈጠረው ሁኔታ ፊፋ ኦፊሴላዊ ምርመራ እንዲጀምር።
የግብጽ እግር ኳስ ማኅበርን በደጋፊዎቹ የሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት በፊፋ የዲሲፕሊን ማዕቀፍ መሠረት ተጠያቂ እንዲያደርግ።
ወደፊት በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ የብሔራዊ ቡድኖች መዝሙሮች በተገቢው መንገድ እንዲከበሩ እና ተንቀሳቃሽ መብራት ተይዞ እንዳይገባ እና ቁጥጥሩ እንዲጠብቅ የሚያስችሉ ርምጃዎችን እንዲወስድ ነው በጻፈው ደብዳቤ የጠየቀው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት፦
Next article“ኢትዮጵያ በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት በርካታ እመርታዊ ለውጦችን አስመዝግባለች” የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት