
ደሴ: ጳጉሜን 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምሥራቅ ሪጂን በደሴ ከተማ አሥተዳደር ለተማሪዎች የደብተር ድጋፍ አድርጓል።
የኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምሥራቅ ሪጂን የሽያጭ ማናጀር ፎዚያ መኮንን ኢትዮ ቴሌኮም የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት “ለነገ ተስፋዎች” በሚል መርሐግብር ለተማሪዎች የደብተር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ተቋሙ በመላው የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚገኙ እና አነስተኛ ገቢ ላላቸው የማኀበረሰብ ክፍሎች ድጋፉን እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ከ373 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከ320ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ድጋፍ መደረጉንም ገልጸዋል።
የሰሜን ምሥራቅ ሪጅንም በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በሦሥት ከተማ አሥተዳደሮች ለሚገኙ ተማሪዎች 3ሺህ 850 ደርዘን ደብተር ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
ድጋፉ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የማኀበረሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ መኾኑን የተናገሩት ወይዘሮ ፎዝያ ዛሬ በደሴ ከተማ በጡንጂት አምባ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 543 ደርዘን ደብተር ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ አብዱልአዚዝ ሁሴን በከተማዋ የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት የሚቸገሩ በርካታ ወገኖች እንዳሉ ገልጸዋል።
ለሚቸገሩ ተማሪዎች ከትምህርታቸው እንዳይደናቀፉ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ተወካይ ኀላፊው ኢትዮ ቴሌኮም እና ሌሎች ድርጅቶች ድጋፍ ማድረጋቸው የሚመሠገን እንደኾነም ተናግረዋል። ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የጡንጂት አምባ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አረጋ ታደሰ በትምህርት ቤቱ በርካታ ተፈናቃይ ተማሪዎች በመኖራቸው የተደረገው የትምህርት የቁሳቁስ ድጋፍ የወላጆችን ጭንቀት ያስወገደ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን