
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከስምንት ዓመታት በፊት በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተው የእምቦጭ አረም ከጊዜ ወደ ጊዜ የስርጭት ዓድማሱ እየሰፋ በሐይቁ ኅልውና ላይ አደጋ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ አረሙን በጊዜያዊነት እና በዘላቂ ሁኔታ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትም በመንግሥት፣ በማኅበረሰብ ተሳትፎ፣ በድጋፍ ፈንድ እና በምርምር ተቋማት ልዩ ልዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ችግሩ ከትናንቱ ከመሻል ይልቅ እየከፋ መምጣቱ ነው የሚነገረው፡፡ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ ሐይቁን ሙሉ በሙሉ ላለማጣት ዋስትና የሚሆን ነገር ያለ አይመስልም፡፡
የችግሩን አሳሳቢነት የተገነዘቡት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በጉዳዩ ዙሪያ ከሰሞኑ ምክክር አድርገዋል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት መርሻ ጫኔ (ፕሮፌሰር) በአካባቢው ላሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከጣና በላይ አሳሳቢ ጉዳይ እንደሌላቸው ገልጸዋል፤ በኮሮና ቫይረስ ስርጭት የተቀዛቀዘው የእምቦጭ አረም መከላከል ከሰሞኑ በአዲስ መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡
ከሰሞኑ በተካሄደው ምክክር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በተናጠል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለውጥ አለማምጣቱ መወሳቱን ፕሮፌሰር መርሻ ጠቁመዋል፤ የምርምር እና የመከላከል ሥራዎቹን ወጥ በሆነ መንገድ ለመምራት የሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮ በማኅበረሰቡ ችግሮች ላይ ጥናት እና ምርምር አድርጎ የመፍትሔ ሐሳብ ማፍለቅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የምርምር ውጤቶቹን ወስዶ በሥራ ላይ የማዋል ኃላፊነት የሌሎች ተቋማት በመሆኑ ከዚህ ቀደም በሚስተዋሉ የምርምር ሥራዎችን ተረክቦ የመጠቀም ውስንነትም በቀጣይ ይቀረፋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ፕሮፌሰር መርሻ ተናግረዋል፡፡
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መንበሩ ተሾመ አረሙን በሰው ጉልበት ማስወገድ የመጀመሪያ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል፤ በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለተወሰነ ጊዜ ከመቆሙ በፊት የተሻለ እንቅስቃሴ እንደነበር እና ለቫይረሱ ተጋላጭነትን በመቀነስ በዘመቻ መልክ ለማስቀጠል ሥራ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡ ዘመቻው በክልሉ ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተቀናጀ ትብብር የሚመሩት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ 50 የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ መምህራን በሐይቁ ዙሪያ ባሉ አራት ቀበሌዎች ዘመቻውን እያስተባበሩ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር መንበሩ በቀጣይ የሚደረጉ የምርምር ሥራዎችም በጥምረት እና በቅንጅት እንደሚካሄዱም ጠቁመዋል፡፡
ይህ ዘገባ በሰናዳበት ጊዜ ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ አቆራርጠው ወደ ሐይቁ አካባቢ የደረሱት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ሠራተኞችም አረሙን የማስወገዱን ሥራ ተቀላቅለዋል፡፡ የአሁኑ አረም የማስወገድ ዘመቻ ጊዜያዊ መፍትሔ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ግርማው አሸብር ተናግረዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ምርምር የልህቀት ማዕከል ለማደራጀት እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ መምህራኑ በዘመቻ ወደቦታው መምጣታቸው ለምርምር ሥራቸው ግብዓት የሚሆን መረጃ ለማግኘት ምልከታ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡