
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአንድ ጤና ማስተባበሪያ መማክርት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ ላይ ውይይት አድርጓል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ሲያስከትሉ ቆይተዋል ብለዋል።
የኮሮና ቫይረስ ያስከተለውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ለአብነት አንስተዋል። እነዚህ በሽታዎች አሁንም ሥጋት መኾናቸውን ነው የገለጹት። ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን፣ የአካባቢ ብክለትን፣ የመድኃኒት መላመድን ለመከላከል መንግሥታዊ፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ በሽታዎች፣ በጸረተባይ እና ሌሎች ኬሚካሎች አጠቃቀም ችግር የሰዎች ህይወት እያለፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከዚህ በፊት በወረርሽኝ የተከሰቱ እንደ ኮሮና ቫይረስ፣ የመተንፈሻ በሽታዎች፣ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ፣ አባ ሰንጋ የመሳሰሉ በሽታዎች የበርካታ ሰዎችን ህይወት ከቀጠፉ በሽታዎች ውስጥ ተጠቅሰዋል።
የአባ ሰንጋ በሽታም በሰሜን ወሎ፣ ዋግኽምራ፣ ሰሜን ጎንደር እና ሌሎች አካባቢዎች ችግር መኾኑን ገልጸዋል። ውሻን የሚያሳብድ በሽታ እና ሌሎች በሽታዎችም የኅብረተሰብ ጤና ችግር መኾናቸውን ነው የገለጹት። ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ችግር እያስከተሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ችግሩን ለመከላከል የአንድ ጤና ምልከታ ትኩረት ተሠጥቶት እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።
የአማራ ክልል እንሰሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ የእንስሳት ጤና ጥበቃ እና ቁጥጥር ተወካይ ዳይሬክተር አሰፋ ረዳኢ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል በአንድ ጤና ምልከታ አማካኝነት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ማኅበረሰቡ እንስሳትን ቀድሞ እንዲያስከትብ፣ በአባ ሰንጋ ምክንያት የሞቱ እንስሳትን እንዳይመገብ እና በአግባቡ እንዲያስወግድ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። ማኅበረሰቡን እንስሳትን በወቅቱ እንዲያስከትብም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:–ዳግማዊ ተሰራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!