ወጣቶች የሀገር ተረካቢነት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።

6
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ወጣቶች ማኅበር 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ አማካሪ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) የአማራ ወጣቶች ማኅበር ላለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ኾኖ በጽናት እዚህ ደርሷል ብለዋል።
ማኅበሩ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች ለመፍታት እና ወጣቶች ከጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች በመራቅ አርቆ አሳቢ እንዲኾኑ የሚሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ወጣቶች ሀገር ተረካቢዎች ናቸው ያሉት አማካሪው የወጣቶችን ውሳኔ ሰጭነት እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ሁሉም በየአካባቢው ያለውን ጸጋ በመጠቀም የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት። የወጣቶችን የዴሞክራሲ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባም አንስተዋል።
ወጣቶች ለክልሉ የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ የልማት ዕቅዱ ትግበራ እና ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ ጉባዔው የወጣቶችን አቅም በመጠቀም ለሰላም እና ለልማት ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ለማድረግ የተዘጋጀ ነው ብለዋል። ማኅበሩ ወጣቶችን እንዴት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ አለበት ለሚለው ግብ ትኩረት መስጠት ይገባዋል ነው ያሉት።
በልዩ ልዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ የወጣቶች ተሳትፎ እያደገ ነው ያሉት ኀላፊው በአንድ ዓመት ብቻ 7 ቢሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብ፣ የጉልበት እና የዕውቀት አስተዋጽኦ ለማኅበረሰቡ አበርክተዋል ብለዋል።
ይህም ወጣቶች ሲደራጁ ለማኅበረሰቡ የሚሰጡት ጠቀሜታ ከፍተኛ መኾኑ የታየበት እንደኾነ ነው የገለጹት። ወጣቶች የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊ አቅም በማጠናከር ተደማጭነታቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የክልሉ የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት እቅድ የወጣቶችም በመኾኑ በአግባቡ እንዲሳተፉ ይጠበቃል ነው ያሉት። ክልሉ እንዲበለጽግ ሚናቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ወጣቶች እርስ በእርስ ተደማምጠው፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አቅማቸውን በማሳደግ ለክልሉ ሰላም የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የአፍሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት ሕዝቦች በቦታ የተራራቁ ግን በታሪክ እና ማንነት የተዋሃዱ ናቸው” አቶ አደም ፋራህ
Next articleከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከልከል የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር ይገባል።