
አዲስ አበባ: ጳጉሜን 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ እና የካረቢያን ሀገራት የጤና ሚኒስትሮች ሥብሠባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የካረቢያን ሀገራት ኅብረት (ካሪኮም) ዋና ጸሐፊ ካርላ ባርኔት የካሪቢያን ሀገራት ኅብረት የዛሬውን ውይይት ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ ይጠቀምበታል ብለዋል።
ውይይቱን ሀገራት በጋራ እያመጡት ያለውን ዕድገት ለማፋጠን፤ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት፣ ለሕዝቦች ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን እና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚጠቀሙበትም ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የካሪኮም አፍሪካ ሀገራት ጉባኤ የአፍሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት ኅብረት አሁንም እንዳለ የሚያስታውስ አዲስ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
በታሪክ እና በጽናት የተሳሰረው የአፍሪካ እና የካሪቢያን ሕዝቦች የጋራ ፈተናዎች እንደገጠሟቸውም አብራርተዋል።
ሀገራቱ አንድ ላይ ተሠባሥበው ለፍትሐዊ የጤና ተደራሽነት መትጋት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት የዘመናት የጋራ ትግልን ወደ አንድ ወጥ ስትራቴጂ መለወጥ ያስፈልጋልም ብለዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ውይይቱ የዲፕሎማሲ ጉዳይ ብቻ ሳይኾን ጠንካራ ትስስር ያላቸው ሕዝቦች ውይይት እንደኾነ ጠቁመዋል።
በቦታ የተራራቁ ግን በታሪክ እና ማንነት የተዋሃዱ ሕዝቦች መድረክ መኾኑንም ተናግረዋል።
በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰት ጎርፍ፣ ድርቅ ተላላፊ እና ተለዋዋጭ የበሽታ ዓይነቶች የአፍሪካ እና የካረቢያንን ሀገራት ዕድገት እያዘገየ ነው ብለዋል።
አፍሪካ እና ካሪቢያን ምንም እንኳን ለዚህ ችግር ምክንያት ባይኾኑም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ኾነዋል ነው ያሉት።ለአየር ንብረት ለውጥ ፍትሕ መጠየቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ዓለማቀፍ ጉባኤ ላይ የተገቡት ቃል ኪዳኖች እንዲፈፀሙ መተባበር ይገባናል ብለዋል።
ወደፊት ባሕላዊ እና ታሪካዊ ትስስርን ወደ ፖለቲካዊ ኀይል እና ኢኮኖሚያዊ አጋርነት በመለወጥ ጠንካራ አጋርነትን ማምጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አዲሱ ዳዊት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን