
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በሁሉም መስክ ፅኑ መሠረት ያላት ብርቱ ሀገር የመገንባት ተግባራችንን እየከወን ነው ብለዋል።
ዛሬ የጽናት ቀንን ምክንያት በማድረግ በላባቸውና በትጋታቸው ሀገር እያፀኑ ከሚገኙ አምራቾች መካከል በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በማዕድን ዘርፍ የተሰማራውን የኤ. ኤም.ጂ ሆልዲንግ የሥራ እንቅሰቃሴዎችን ተዘዋውረን ተመልክተናል ነው ያሉት።
ሀገር በቀሉ የግል ኩባንያ ጥራታቸውን የጠበቁ የብርታ ብረት፣ የመስታወት፣ የቡና ምርትና የወጪ ንግድ፣ የግብርና ምርቶች በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ለኢትዮጵያ ልዕልና የድርሻውን አሻራ እያሳረፈ ነው።
ኩባንያው ለኮሪደር ልማቱ የሚሆኑ ከውጪ የሚገቡ ስማርት ፖሎችን በማምረትና በመተካት ረገድም ትልቅ ሚና እየተወጣ ይገኛል። ሀገራችን እና አርሶ አደሮቻችን ከቡና ወጪ ንግድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ኤ. ኤም.ጂ ሆልዲንግ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው።
በግል ኢንዱስትሪ ፓርኩ የተመለከትናቸው ተግባራት የመንግሥታችንን የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ በማሳካት ረገድ የግሉ ዘርፍ ዋነኛ አንቀሳቃሽ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል። በጀግኖች ደም የፀናች ሀገር በልማት አርበኞቿ የልዕልና ጉዞዋን ታሳካለች።
መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አልሚዎች የተኪ ምርትና የወጪ ንግድ ምርትን በማሳደግ በብርቱ ሀገር ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
