
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ “ጽኑ መሠረት ብርቱ ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት የጽናት ቀንን በልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች አክብሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ነጻነት በሁሉም ዜጎች የሚጠበቅ የታማኝነት፣ የቁርጠኝነት እና “ለሀገር ሉዓላዊነት የሚከፈል የመስዋዕትነት ማረጋገጫ ነው” ብለዋል።
ነጻነት እና ጽናት የሚገለጸው በአጥንት እና በደም በሚከፈል ሐቀኛ እና እውነተኛ መሥዋዕትነት ነው ብለዋል። በጽናት የሚኖሩት እና የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ከውስጥም ኾነ ከውጭ በመስዋዕትነት እየጠበቁ የሚገኙት የጸጥታ አካላት ናቸው ብለዋል።
የዛሬው የጽናት ቀን ሲከበር ከሁሉም በላይ ለመላው የፖሊስ አባላት እና የሠራዊቱ አባላት ትርጉሙ የተለየ እንደኾነ ነው የገለጹት። የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት መከበር የሚረጋገጠው ሠራዊቱ በሚከፍለው የደም እና የአጥንት መስዋዕትነት እንደኾነም ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ጽናት የሚረጋገጠው የሀገራቸውን ችግር ለመፍታት ትክክለኛውን መነሻ ምክንያት መሠረት አድርገው በሚጠይቁ ዜጎች እና በሚያስቀምጡት መፍትሔ እንዲሁም ለመፍትሔው በሚከፍሉት መስዋዕትነት ነው ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ ተገንብቶ ከዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከሁሉም በላይ የጸጥታ ኃይሉ ሚናው ላቅ ያለ መኾኑንም አንስተዋል። ለከፈሉት መስዋዕትነትም ምስጋና አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) ጽናት የሠራዊታችን ዋና መለያ ነው ብለዋል። በርካቶች የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ መሥዋትነት ከፍለዋል፤ ቀን ከሌሊት እየተጉም ይገኛሉ ነው ያሉት።
ሁሉም የሀገራችን የጸጥታ አካላት በየተመደቡበት በቁርጠኝነት ጸንተው ሀገራቸውን አቆይተዋል ብለዋል። እኛም ሀገራችንን በከፍታ የምንጠብቅበት እንደኾነ ነው የገለጹት። የሕዳሴ ግድቡን እየጠበቁ በመስዋዕትነት ለዚህ ላደረሱት በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ሀገር በሁሉም ሰው ይለማል ያሉት ኮሚሽነሩ ሀገራችን የብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር መላው የጸጥታ አካላት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል። የጽናት ቀን ሀገራችን የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ የምናስቀጥልበት እና ለሕዝብ ቃል የምንገባበት እንደኾነ ነው የተናገሩት።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሎጀስቲክስ አሥተዳደር መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ታዬ ኃብተ ጊዮርጊስ ቀኑን ስናከብር አባቶቻችን ለሀገር የከፈሉትን መስዋዕትነት በማሰብ ነው ብለዋል።
የጽናት ቀንን ስናከብር የታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሚጠናቀቅበት ወቅት በመኾኑ የተለየ ትርጉም ያሰጠዋል ነው ያሉት። ለሕዝብ የገባነውን ቃል የምናከብርበት እና ከልብ በመነጨ መንገድ መስዋዕትነት እየከፈልን የምንቀጥልበት እንደኾነም ነው የገለጹት።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የማኀበራዊ አገልግሎት መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አየሁ ታደሰ የጽናት ቀን የሀገርን ዳር ድንበር ለመጠበቅ እየተዋደቁ ለሚገኙት የጸጥታ እና የሠራዊት አባላት ልዩ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።
ቀኑ በጽናት ተሰይሞ መከበሩ የጸጥታ አካላት ከፊት ኾነው እየከፈሉት ያለው መስዋዕትነትን ለማሰብ መኾኑንም ገልጸዋል። በቀጣይ በበለጠ ትጋት እና ጽናት ለተሻለ ግዳጅ የሚያነሳሳ እንደኾነም ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
