ኢትዮጵያ በጽናት ጸንታ የኖረች ሀገር ናት።

3
ገንዳ ውኃ: ጳጉሜን 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ጳጉሜን አንድ “የጽናት ቀን” የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የመደበኛ ፖሊስ አባላት እና የአድማ መከላከል ፖሊስ በተገኙበት ተከብሯል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ተወካይ አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ደረሰ አዱኛ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት የተለየ የሚያደርጋት የቀን አቆጣጠሯ ነው። እንደሀገር የሚከበሩትን የጳጉሜን ቀናቶች በተለያዩ ኹነቶች እንደሚያከብሩ ተናግረዋል።
ጳጉሜን 1/2017 ዓ.ም የጽናት ቀን መሰዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን በማስታወስ በዓሉ እየተከበረ እንደኾነም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ የኖረች እና ሉዓላዊነቷን የማታስደፍር ሀገር ነት ያሉት ኀላፊው ይህም የጽናት ተምሳሌት ለመኾኗ ማሳያ እንደኾነ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በደም እና በአጥንት የተከበረችውን ያህል በላብም ብልጽግናን የምታረጋግጥ ሀገር እንድትኾን ታልሞ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የሰሜን ምዕራብ መምሪያ ሪጅመንት ስድስት አዛዥ ኮማንደር ቢራራ ተባባል የጽናት ቀን ሲከበር ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ያለፈችባቸውን ውጣ ውረዶች ወደ ኃላ መለስ ብሎ ለማየት እንደሚያግዝ ነው የጠቆሙት።
ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮችን እና መከራዎችን አልፋ በጽናት ጸንታ የኖረች ሀገር እንደኾነችም ጠቅሰዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ምሥጋናው ካሴ የጽናት ቀን ሲከበር ለሀገር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች የሚታወሱበት እንደኾነም ተናግረዋል።
በቀጣይም በጽናት በመቆም ለሀገር ዋጋ በመክፈል ኢትዮጵያን ለማሳደግ ዝግጅት የሚደረግበት በዓል እንደኾነ ተናግረዋል።
የጽናት ቀን የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እና በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ለማርገብ ትልቅ መነሳሳት ይፈጥራል ነው ያሉት።
ትውልድን ለመቅረጽም የጽናት ቀን ሚናው የጎላ እንደኾነ አስገንዝበዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ504ኛ ኮር አባል መቶ አለቃ አበበ ሙሉጌታ ጽናት ከአባቶች የቆየ መኾኑን ገልጸዋል።
ጽናት በችግር ውስጥም ተኹኖ የተሠሩ ሥራዎች ለትውልድ የሚተላለፉበት እንደኾነም አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጽኑ ፍላጎታችንን ለዓለም ያሳየ ነው።
Next article“ጽናት ለሀገር ሉዓላዊነት የሚከፈል የመስዋዕትነት ማረጋገጫ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)