ጽናት ለፀጥታ ተቋማት የአሸናፊነት ኃይል ነው።

0
ደብረ ብርሃን: ጳጉሜን 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጽናት ቀን “ጽኑ መሠረት፣ ብርቱ ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ብርሃን ከተማ ተከብሯል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ተወካይ እና የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኀላፊ ዳንኤል እሸቴ በደብረ ብርሃን ከተማ ሰላም እንዲሰፍን ላደረገው የጸጥታ መዋቅሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም “ያገኘነውን አንጻራዊ ሰላም ማጽናት ዋነኛ ተግባራችን ይኾናል” ብለዋል፡፡ በከተማው አልፎ አልፎ የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅም አሳስበዋል፡፡
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ112ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር ዘመቻ መምሪያ ኀላፊ ሻምበል ታዲዎስ ኢሳያስ ጽናት ለፀጥታ ተቋማት የአሸናፊነት ኃይል መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሉ በቀጣይም በዓላማ ጽናት የሚሰጠውን ተልዕኮ እና ግዳጅ በብቃት መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ቀኑ በብሔራዊ ጥቅማችን እና ሀገራዊ አንድነታችን የማንደራደር መኾናችንን በጽናት የምናሳይበት ዕለት ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ ክልሉ አጋጥሞት ከነበረው አለመረጋጋት ለማውጣት በተደረገ የጽናት ትግል ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ይህ ሰላም ይገኝ ዘንድ ክልሉ ችግር ውስጥ በነበረበት ወቅት ከፌዴራል እስከ ታችኛው እርከን የሚገኙ የፀጥታ መዋቀር አካላት ለከፈሉት ዋጋ በዚህ የጽናት ቀን ልናመሰግናቸውን ይገባል ብለዋል፡፡
ጽናት ለወታደር ትልቅ ትርጉም አለው ያሉት ምክትል ኀላፊው የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን ሁሉ በጽናት በማለፍ አመርቂ ድል እያስመዘገበ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
አንድነታችን ለጋራ ሕልውናችን መቀጠል አስፈላጊ ነው ብለዋል። የጸጥታ ችግሮችን በጽናት መታገል እና ማስወገድ የቀጣይ ቁልፍ ተልዕኮ መኾኑንም አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወልድያ ዲስትሪክት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።
Next articleሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጽኑ ፍላጎታችንን ለዓለም ያሳየ ነው።