
ደብረ ማርቆስ: ጳጉሜን 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ2017 ዓ.ም የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች መከበር ጀምረዋል።
ጳጉሜን 01 የጽናት ቀን “ጽኑ መሠረት፣ ብርቱ ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አበበ ደለለ የጽናት ተምሳሌት የኾነው የታላቁ “ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ዋዜማ ላይ ኾነን የጽናት ቀንን ማክበራችን ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው” ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ክልሉ ያጋጠመውን የሰላም እና ፀጥታ ፈተናዎች ለመመከት እና ሰላምን ለማረጋገጥ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት በጽናት ታግለናል ነው ያሉት።
ነገን የበለጠ የተሻለ ለማድረግ እና ሰላምን ለማጽናት በቀጣይ ለቆምንለት ዓላማ በጽናት መታገል እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ ኮሎኔል ዝናቡ ልመንህ ዳግማዊ ዓድዋ በኾነው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የታየውን አንድነት በማጠናከር የፀጥታ አካላት እንደ ሀገር አንድ ኾነን ሀገር በጠላት እንዳትደፈር ዝግጁነታችንን የምናረጋግጥበት ቀን ነው ብለዋል።
በበዓሉ የታደሙ ሌሎች የፀጥታ አካላትም በፈተናዎች ውስጥ አልፈን በጽናት በመታገላችን ተስፋ ሰጭ የሰላም ሁኔታ እንዲታይ አድርገናል ነው ያሉት።
በቀጣይም የሕዝቡን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንሠራለን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ለሀገር ክብር እና ሰላም መጠበቅ ሁሉም አንድ ኾኖ እንዲቆም በበዓሉ ላይ መልዕክት ተላልፏል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!