
ከሚሴ: ጳጉሜን 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ጳጉሜን 1/2017 ዓ.ም የጽናት ቀን በሚል ስያሜ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚሴ ከተማ ዕለቱን የከተማው ነዋሪዎች፣ በከተማው የሚገኙ የጸጥታ መዋቅር አባላት እና መሪዎች በከተማ ጽዳት እና በተለያዩ ሁነቶች እያከበሩት ይገኛሉ።
በከተማው የሚገኙ የጸጥታ መዋቅር አባላት እና መሪዎች ባለፈው ዓመት እንደሀገር ብዙ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም በጽናት በመቆም በርካታ ስኬቶች ማስመዝገባቸውን ነው የተናገሩት።
ጳጉሜ 1/2017 ዓ.ም የጽናት ቀን ሲከበር ለሀገር ክብር በአንድነት በመቆም ሊኾን እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኹሉም የጸጥታ መዋቅር አባላት እና መሪዎች የሀገር ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በአዲሱ ዓመት በፈተናዎች ሳይንበረከኩ በጽናት ከሕዝብ ጋር እንደሚቆሙም ተናግረዋል።
የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ሳዳም ሁሴን ዕለቱን በከተማ አሥተዳደሩ ከሚገኙ የጸጥታ መዋቅር አባላት ጋር እያከበሩ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ሀገር የምትቀጥለው ለሀገር ሉዓላዊነት ክብር ሁሉም በጽናት መቆም ሲችል ነው ብለዋል። ለሀገር ሰላም እና ልማት በትብብር መቆም እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የከተማ አሥተዳደሩን እና የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ የተቻለው ማኅበረሰቡን እና የጸጥታ መዋቅሩን በማቀናጀት በጽናት በመሠራቱ መኾኑን ገልጸዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ አወል እንድሪስ ከዚህ ቀደም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አጋጥሞ የነበረውን የሰላም ችግር መቅረፍ የተቻለው ከማኅበረሰቡ እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጽናት በተሠራው የሰላም ግንባታ ሥራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ሰላምን በማጽናት የመልማት ፍላጎትን ለማሳካት በአንድነት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን