የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ትናንት ተጀምሯል፤ ዛሬም ቀጥሎ እንደሚውል ታውቋል፡፡

293

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌት እና ዓመታዊ የውኃ አለቃቅ በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል የሚደረገው የሦስትዮሽ ድርድር ተካሂዷል፡፡ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ገጹ እንዳስታወቀው ትናንት ሰኔ 02 ቀን 2012 ዓ.ም በበይነ-መረብ (ቪዲዮ ኮንፈረንስ) ታዛቢዎች በተገኙበት በውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ነው ድርድሩ የተካሄደው።

ድርድሩን ደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ ታዝበውታል።
በዚህ ድርድር ሀገራቱ የድርድር ሥነ-ሥርዓትን፣ ታዛቢዎችን፣ ስለድርድሩ አካሄድ እና ዋናዋና የድርድር ያልተቋጩ ጉዳዮችን በተመለከተ ተነጋግረዋል። እያንዳንዳው ተደራዳሪ ሀገራት ዋና ዋና የድርድር ጉዳዮች ናቸው ያሏቸውን ሐሳቦች በዝርዝር አቅርበዋል።

በዚህም መሠረት በቀጣይ ቀናት ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ይሁን እንጂ የታዛቢዎቹ ሚና ምን ይሁን የሚለውን በተመለከተ በሀገራቱ መካከል መግባባት ላይ አለመደረሱን ነው ያመለከተው፡፡ ውይይቱ ዛሬም የሚቀጥል እንደሆነም ተመላክቷል።

የሦስቱ ሀገራት ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ የውኃ ሙሌት እና ዓመታዊ አለቃቅ ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሚሆንም የውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስር መግለጫ ያሳያል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ልዩነቶችን በድርድር ለመፍታት ኢትዮጵያ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዝግጁ መሆኗንም አስታውቃለች።

Previous articleበቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ወቅቱን ወደ ጥሩ እድል በመቀየር እንዲጠቀሙበት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮው አሳሰበ፡፡
Next articleየአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮ-ሱዳን የባቡር ፕሮጀክት የአዋጭነት ጥናት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አጸደቀ፡፡