የአሸናፊነት ትልቁ ምስጢር ጽናት ነው።

1
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጳጉሜ 01/2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የጽናት ቀን ኾኖ እየታሰበ ነው። ጽናት ከአቋም ፍንክች አለማለትን፣ በአቋም መጽናትን እና አለማወላወልን የሚያመለክት መዝገበ ቃላዊ ትርጉም አለው፡፡
“የአሸናፊነት ትልቁ ሚስጥር ጽናት ነው” እንዳሉት ቪክቶር ኢውጎ የተባሉ ፈረንሳዊ ጸሐፊ በተመሳሳይ ሙያ 51 ዓመታትን በፍቅር ካሸነፋ መምህር ጋር አሚኮ ያደረገነውን ቆይታ እናጋራችሁ።
መምህር አብርሃም መከተ ይባላሉ። ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች 40 ዓመታትን፤ በግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ 11 ዓመታትን በጽናት ወገናቸውን አገልግለዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንግሊዝኛ ቋንቋን አስተምረዋል። አሁን ላይ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው አዞል አካዳሚ በማስተማር ሙያ ላይ ይገኛሉ።
ትምህርት ከመጀመራቸው ከ1956ዓ.ም በፊት በልጅነት አለባበሱን በትኩረት የተመለከቱት መምህር ለሙያው ፍቅር እንዲያድርባቸው ማድረጉን ያስታውሳሉ።
በ1964 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ብቁ መኾናቸው ተረጋግጦ የጅማ መምህራን ማሠልጠኛ ተቋምን በ1965ዓ.ም ተቀላቅለዋል።
ለሁለት ዓመት የመምህርነት ሙያን አጥንተውም በ1966 ዓ.ም መጨረሻ ተመርቀዋል። በ1967 ዓ.ም ደግሞ የመምህርነት ሙያን አሀዱ ብለው እንደጀመሩ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
እርሳቸው ማስተማር በጀመሩበት ጊዜ ተማሪዎችን ለማብቃት ይሰጥ የነበረው ትምህርትም እጅ ሥራ፣ እርሻ፣ ጎጆ ኢንዱስትሪ እና ኑሮ በዘዴ እንደነበረም ነግረውናል።
ጫካ ውስጥ በመግባት ቅጠል እየቀነጠሱ፣ አፈር እየቆፈሩ፣ ፊደላትን እየቀረጹ፣ ጭቃ ጠፍጥፈው የመገለገያ ቁሳቁሶችን በሸክላ እየሠሩ በጽናት ሲያስተምሩ እንደነበረም ገልጸውልናል።
የመምህርነት ሙያም በወቅቱ እጅግ የተከበረ ሙያ እንደነበረ መምህር አብርሃም ያስታውሳሉ። ጥሩ ጊዜን በሙያው ላይ እንዳሳለፉም ነግረውናል። 51 ዓመታትን በተመሳሳይ ሙያ በጽናት የማለፋቸው ሚስጥርም ይኸው ጉዳይ እንደኾነ መገመት አይከብድም። አሁን ላይ ያለው የመምህርነት ሙያ ክብር ከበፊቱ አንጻር ሲታይ ውስንነት እንዳለውም ትዝብታቸውን አጋርተውናል።
ከተማሪዎች ሥነ ምግባር አንጻር ላነሳንላቸው ሃሳብም እርሳቸው በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ለመምህራን ክብር እና ፍቅር የሚሰጡ ምስጉን ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ጥቂት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ባቀኑባቸው አጋጣሚዎች መምህር ለመደባደብ ልብሳቸውን ከእጃቸው ከፍ ከፍ የሚያደርጉ እና ሌሎች የሥነ ምግባር ጥፋቶች ሲፈጥሩ የተመለከቷቸው አንገት የሚያስደፋ ጥቂት ተማሪዎች መመልከታቸውን አነሱልን።
የጽናት ተምሳሌት የኾኑት መምህር አብርሃም ብዙ ዓመታትን በብዙ የሥራ ቦታዎች ከብዙ ሰዎች ጋር በጽናት አሳልፈዋል።
መምህራን ትምህርት ብቻ ሳይኾን ሥነ ምግባርም ነው የሚያስተምሩት፤ ለመጭው ትውልድ ተማሪዎችን የሚያበቁ፣ የሀገር ሃብት፣ ከተከበሩ እና ፍቅር ከተሰጣቸው ያላቸውን ነገር አሟጠው በማስተማር ልጆችን የሚያበቁ መኾናቸው መረሳት የለበትም ይላሉ።
በትምህርት ውጤት እንዲመጣ ጥረት የሚያደርጉ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ቢኖሩም እየተመዘገበ ያለው ውጤት እንደሚጠበቀው እና እንደሚታሰበው እንዳልኾነ ገልጸዋል።
ትምህርት ቤት መምህሩን ነው የሚመስል ያሉት መምህር አብርሃም የትምህርት ጥራት ችግር ከመምህራን እና ከተማሪዎች ጥረት ውስንነት፣ ከብዙ ተማሪዎች የቤተሰብ ክትትል ውስንነት፣ ተምረው በአጥጋቢ ሁኔታ ሥራ ከማግኘት፣ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የተፈጠረ እንደኾነም የግል አስተያየታቸውን ጠቁመዋል።
መፍትሔውም ሁሉም ባለ ድርሻ አካል በጽናት የተለየ ጥረት እና ትግል ማደረግ ነው ብለዋል።
መምህራን በመጀመሪያ የሚያስተምሩትን ትምህርት እና ሙያውን ወደውት እና አምነውበት ሊገቡ እንደሚገባ ገልጸዋል። ለትውልድ ከፍተኛ የኾነ መስዋዕትነት ሊከፍሉ እንደሚገባም አሳስበዋል። እርሳቸው ለወገናቸው እና ለሙያው ሊሰጠው ከሚገባው ትኩረት አንጻር በተመሳሳይ የሙያ ጽናት 51 ዓመታትን መስዋዕት ከፍለዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመንም የሚጠበቅባቸውን ተግባራት ለመከወን እና 52ኛ ዓመትን በጽናት የማስተማር ጊዜያቸውን ለመቀጠል ከወዲሁ ዝግጀት ላይ ናቸው።
ያላቸውን ጉልበት አሟጠው በመጠቀም ለሌሎች መምህራን ትምህርት አስተላልፈው ለማጠናቀቅ ማሰባቸውንም በወኔ ገልጸውልናል። ጽኑ መምህር! ጽኑ የዕውቀት አባት! ጽኑ የሙያ ፍቅር! ጽኑ የወገን ፍቅር! ጽኑ የዕድሜ መስዋዕትነት በመምህር አብርሃም ተገልጧል።
ዘጋቢ:- ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጽናት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተከበረ።
Next articleየጽናት ቀን በከሚሴ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው።