
ባሕር ዳር: ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አውደ ጥናት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አንዷለም ጤናው የትብብር መድረኩ በ2013 ዓ.ም ከተመሠረተ ጀምሮ ከተሜነትን ለማስፋፋት እና ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲኾኑ እየሠራ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ 113 የኢትዮጵያ ከተሞች በአባልነት እየተሳተፉ እንደሚገኙ አንስተዋል። ከአማራ ክልል 32 ከተሞችም የትብብር መድረኩ አባል መኾናቸውን ጠቁመዋል።
የትብብር መድረኩ አባል ከተሞች የልምድ ልውውጥ፣ የዕውቀት ሽግግር፣ የመማማሪያ እና የመግባቢያ መድረክ በመፍጠር አቅማቸውን ማሳደግ ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
ያልተመጣጠነ እድገትን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የተለየ ስልት ነድፎ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ከተሞች ጋርም በጋራ እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ነው ብለዋል።
ለከንቲባዎች እና ሥራ አሥኪያጆች አቅማቸውን ለማሳደግ ሥልጠናዎችን እየሠጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በባሕር ዳር የተካሄደው አውደ ጥናት በክልሉ የሚገኙ ከተሞች አቅማቸውን በማሳደግ በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ የዓለም ዓቀፍ ተሞክሮዎችን ለማካፈል የሚያስችል ነው ብለዋል።
አማራ ክልል ካለው የቆዳ ስፋት እና የከተማ ብዛት አንጻር የክልሉ ከተሞች የትብብር መድረኩ አባል በመኾን አብረው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ከተማዋ የትብብር መድረኩ መስራች መኾኗን ተናግረዋል። የትብብር መድረኩ በከተማዋ እየተሠሩ ላሉ እና በቀጣይም ለሚሠሩት የልማት ሥራዎችን እያሳለጠ ነው ብለዋል።
በከተሞች ያሉትን ክፍተቶች በጥናት በመለየት፣ መሪዎች የውጭ ሀገር ተሞክሮዎችን እንዲያመጡ በማመቻቸት፣ በከተማ ልማት የተሠማሩ ምሁራንን እየጋበዘ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንም እየሰጠ መኾኑንም አመላክተዋል።
የትብብር መድረኩ ከተሞች በገቢ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ፣ ልምድ እንዲለዋወጡ፣ ተሞክሮ እንዲያመጡ እያስቻለ መኾኑን ነው የገለጹት።
የሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ እንኳይነህ ሙሉ የሁመራ ከተማ የኢትዮጵያ ከተሞች አባል መኾኗን ገልጸዋል። በከተማዋ ያለውን ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀም የትብብር መድረኩ አጋዥ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ምቹ መኾኗን ያነሱት ከንቲባው በትብብር መድረኩ በአባልነት መሳተፍ የተሻለ የከተማ ልማት ሥራዎችን ለማከናወን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ የትብብር መድረኩ አባል በመኾናቸው የተለያዩ የሀገር ውስጥ ከተሞችን ልምድ ለመቅሰም እንዳስቻለ ተናግረዋል።
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በከተሞች ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶችን በሥልጠና እየተሰጠ በከተማ ልማት ዙሪያ አቅም ለመገንባት እድል ፈጥሮልናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!