ኢትዮ ቴሌኮም ደብረ ብርሃን ለሚገኘው ሐበሻ አረጋውያን እና ምስጉኖች መርጃ ልማት ድርጅት ድጋፍ አደረገ።

5
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም ማዕከላዊ ሰሜን ሪጅን ደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኘው የሐበሻ አረጋውያን እና ምስጉኖች መርጃ ልማት ድርጅት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
በኢትዮ ቴሌኮም የማዕከላዊ ሰሜን ሪጅን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አንተነህ ፋንታሁነኝ ተቋሙ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ለሐበሻ አረጋውያን እና ምስጉኖች መርጃ ልማት ድርጅት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡
መጭውን 2018 አዲስ ዓመት መሠረት በማድረግ ደግሞ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።
“በኢትዮ ቴሌኮም ማዕከላዊ ሰሜን ሪጅን በበጀት ዓመቱ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በመወጣት በኩል በርካታ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ መቆየቱን” አቶ አንተነህ አንስተዋል፡፡
በዚህም 39 ለሚኾኑ በጎ አድራጎት ማኅበራት ከ47 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
ከ13 ሺህ 600 በላይ ወገኖች የድጋፉ ተጠቃሚ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት።
የሐበሻ አረጋውያን እና ምስጉኖች ልማት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ዮርዳኖስ ፈቃዱ “ኢትዮ ቴሌኮም ለድርጅታችን ላደረገው ድጋፍ ከልብ እናመሰግናለን” ብለዋል። ሐበሻ አረጋውያን በታሪኩ በአንድ ተቋም ትልቁ ድጋፍ ሲደረግለት ይህ የመጀመሪያው መኾኑን አንስተዋል፡፡
ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት በቋሚነት፣ በቤት ለቤት እና በተመላላሽ ከ500 በላይ አረጋውያን እና ምስጉኖችን ድጋፍ እያደረገ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ በበጀት እጥረት እየተፈተነ ባለበት በዚህ ሰዓት ኢትዮ ቴሌኮም ያደረገው ድጋፍ የተለየ ትርጉም አለው ነው ያሉት ሥራ አሥኪያጁ፡፡ በቀጣይም ሌሎች ተቋማት እና ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ: ወንዲፍራው ዘውዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“በአብሮነት እና በኅብረት ተሰልፈን ሰላማዊ ዓድዋን በሕዳሴው ግድብ እውን አድርገናል” አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር)
Next articleከተሞች ለኑሮ ምቹ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው።