“በአብሮነት እና በኅብረት ተሰልፈን ሰላማዊ ዓድዋን በሕዳሴው ግድብ እውን አድርገናል” አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር)

7
አዲስ አበባ: ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በማስመልከት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው።
የፓናል ውይይቱ “በኅብረት ችለናል”በሚል መሪ መልእክት ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በውይይቱ መልእክት ያስተላለፉት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ
የማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) አፈራችንን እና ማዕድናችንን ሲወስድ ለሺህ ዓመታት ቆመን ስናየው የኖርነው እና የቁጭታችን ምክንያት የነበረው ዓባይ እንደፈረስ መጋለቡን ትቶ ለሀገሬው ልማት እንዲውል በዚህ ትውልድ ተሠርቷል ብለዋል።
ይህ ትውልድ በታታሪነቱ በልማት ማሸብረቅ የቻለበትን እድል በሕዳሴው ግድብ ማግኘቱንም አብራርተዋል።
በአብሮነት እና በኅብረት ተሰልፈን ሰላማዊ ዓድዋን በሕዳሴው ግድብ እውን አድርገናል ብለዋል። ይሄን እውን ለማድረግ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም መንግሥት እና ሕዝብ በጋራ ፀንተዋል ብለዋል።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትም ለሕዳሴ ግድቡ መሳካት ከአጋር ተቋማት ጋር በመቀናጀት፣ ሕዝብን በማሰባሰብ እና በማስተባበር የበኩሉን ድርሻ በቁርጠኝነት መወጣቱንም ተናግረዋል።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ ሞቱማ መቃሳ ዓባይን ለመጠቀም ያለፈው ትውልድ የበኩሉን ጥረት ያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል። ነገር ግን በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት አልተሳካም ነው ያሉት። ይህ ትውልድ ደግሞ አብሮ እና ቆርጦ በመነሳት የዘመናት ቁጭቱን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቋጭቷል ብለዋል።
ለዚህ ግድብ እውን መኾን ተሳትፎ ያላደረገ ዜጋ የለም ያሉት አማካሪው ኅብረትና አብሮነት እንደዚህ የገዘፉ ታሪኮችን ለመሥራት መሠረት መኾኑን ያሳያል ብለዋል።
ይሄን አስተምሮ በመከተል በቀጣይም ለሚተገበሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች እውን መኾን ኅብረትን አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ መኾኑን አንስተዋል።
ዘጋቢ:- አዲሱ ዳዊት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleከተሞች ለፈጠራ እና ኢኖቬሽን ምቹ እንዲኾኑ መሥራት እንደሚገባ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) አሳሰቡ።
Next articleኢትዮ ቴሌኮም ደብረ ብርሃን ለሚገኘው ሐበሻ አረጋውያን እና ምስጉኖች መርጃ ልማት ድርጅት ድጋፍ አደረገ።