ከተሞች ለፈጠራ እና ኢኖቬሽን ምቹ እንዲኾኑ መሥራት እንደሚገባ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) አሳሰቡ።

4
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ዐውደ ጥናት እያካሄደ ነው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ የከተማ መሪ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ተናግረዋል።
ከተሞች የልምድ ልውውጥ በማድረግ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየተሠራ ያለው ተግባር የሚበረታታ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የትብብር መድረኩ ከተሞችን እያሥተሳሰረ እና ግንኙነታቸውን በማጠናከር በኩል አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ከተሞች ያላቸውን አቅም የሚያሳዩበት ዕድል የፈጠረ መኾኑንም አንስተዋል።
መድረኩ ከተሞች በዓለም ዓቀፍ የከተሞች ደረጃ መሠረት አድርገው እንዲሠሩ ያግዛል ነው ያሉት። በተለይም በዘላቂ ልማት የተቀመጡ ግቦችን ታሳቢ አድርገው እንዲሠሩ እና ለአንድ ዓላማ እንዲቆሙ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
በከተሞች ያለው ጸጋ እና የልማት አቅም ከፍተኛ ነው ያሉት ዶክተር አሕመዲን ሙሐመድ ከተሞች የቴክኖሎጅ፣ የተፈጥሮ እና የሰብዓዊ ሃብቶች መገኛ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ጤናማ የኾነ ዜጋ እና ማኅበራዊ አቅሞች እንዳሉባቸውም ነው የጠቆሙት። ከመሠረተ ልማት አኳያ ውስን የፕሮጀክት አፈጻጸም አቅም፣ የከተሜነት ዕድገት እና መዋቅራዊ ፕላንን ያልተከተለ አሰፋፈር የሚስተዋልባቸው መኾኑን ጠቁመዋል። ይህን ለማሥተካከል እየተሠራ ስለመኾኑም ነው ያመላከቱት።
ታታሪ እና ጤናማ ዜጎች የሚኖሩባቸው፣ ለነዋሪዎች ምቹ የኾኑ ከተሞች እንዲኖሩ ማድረግ ይገባልም ብለዋል። የራሳቸውን ፍላጎት በራሳቸው አቅም እንዲሸፍኑ ማድረግ ይጠበቃልም ነው ያሉት።
ለፈጠራ እና ለኢኖቬሽን ምቹ እንዲኾኑም መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊ እና ለፈጠራ የተመቹ እንዲኾኑ ማድረግ እንደሚጠበቅም አሳስበዋል። ለንግድ፣ ለቱሪዝም፣ ለመዝናኛ ክፍት እንዲኾኑ በቀጣይ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በቀጣይ ከኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ጋር የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ መድረኮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በቅንጅት ይሠራልም ነው ያሉት። የከተማ አመራር አቅም ግንባታ ላይም በቅንጅት እንደሚሠራ አመላክተዋል።
የክልሉን ሁኔታ ያገናዘበ ከአጭር እስከ ረጅም ጊዜ የከተማ ፕላን እና አሥተዳደር ሥርዓት በጥናት እንዲመለስ ሙያዊ ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ እና መልካም አሥተዳደር ጉዳዮችም ተጨባጭ ውጤት የሚያመጡ ተግባራትን በጋራ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል።
በክልሉ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን በማስተሳሰር በኩልም በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአካታችነት ምዘና ላይ ጥሩ የፈጸሙትን ማበረታታት እና ድክመት የታየባቸውን ማገዝ ይገባል።
Next article“በአብሮነት እና በኅብረት ተሰልፈን ሰላማዊ ዓድዋን በሕዳሴው ግድብ እውን አድርገናል” አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር)