
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የሥርዓተ ጾታ እና ማኅበራዊ አካታችነት የተቋማት ምዘና ላይ ውይይት አድርጓል።
ውይይቱ በተቋማት ውስጥ የሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ያለበትን ደረጃ ለመገምገም ያለመ መኾኑን የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ፍትሐዊ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ የልማት ዕቅዶችን እያዘጋጀ ሲኾን ቢሮው ደግሞ እነዚህን ዕቅዶች ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚረዱ የፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ እየሠራ መኾኑን ኀላፊዋ ጠቅሰዋል።
ይህም የሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞችን ከመቸውም ጊዜ በላይ ንቁ ተሳታፊ እና የልማት ውጤቶች ተጠቃሚ እንዲኾኑ የሚያስችል ነው።
በዚህም መሠረት ቢሮው የመንግሥት አካላት ለሚያዘጋጇቸው የአጭር እና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎች እና የልማት ፕሮግራሞች ላይ የሴቶች፣ የሕጻናት እና የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አይተው እና አካትተው እንዲሠሩ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ነው ያሉት።
ይህም በእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ላይ ዋስትና ይሰጣል።
የሴቶችን የውሳኔ ሰጭነት ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት በተለይም ከዩኤን ውመን ጋር በመተባበር የክህሎት ግንባታ ሥልጠናዎች ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።
የዛሬው ውይይትም ተቋማት የሴቶችን፣ ሕጻናትን፣ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን አካትቶ በመተግበር ያሉበትን ደረጃ ለመለየት፣ ክፍተቶችን ለመሙላት እና የተሻለ የሠሩትን ዕውቅና ለመስጠት ያለመ መኾኑን አስረድተዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የዚህ መድረክ ዋነኛ ዓላማ የማኅበራዊ አካታችነት አስፈላጊነትን ከመረዳት በተጨማሪ የተቋማት አፈጻጸም ምን እንደሚመስል በመገምገም ጥሩ የሠሩ ተቋማት እንዲበረታቱ፣ ክፍተት ያለባቸው ደግሞ በስትራቴጂያዊ ዕቅድ እንዲሞሉ ለማስቻል መኾኑን ገልጸዋል።
“ማኅበራዊ አካታችነት ማለት ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስክ ያለምንም አድሎ እና መገለል በነጻነት የሚሳተፍበትን ዕድል መፍጠር ማለት እንጂ ለሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ችሮታ መስጠት አይደለም” ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ።
እንደየ ችሎታቸውም የሥራ ዕድል በመፍጠር እና እገዛ የሚፈልጉትን በመርዳት የአካታችነት ሥራው ሊጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በውይይቱ የ2017 በጀት ዓመት የአካቶ ትግበራ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲኾን ከተሳታፊዎች ጠቃሚ ሃሳቦች እና አስተያየቶች ተነስተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!