ሀገር የምትገነባው በሰው ነው፤ ሰውን የሚሠራው ደግሞ ትምህርት ነው።

5
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ተማር ልጄ…” የሚሉት ቀደምት ኢትዮጵያውያን በትምህርት ላይ የነበራቸውን ጠንካራ ተስፋ ደም እና ሕይዎት፤ ሥጋ እና አጥንት አልብሶ ሕያው ያደርጋቸዋል።
ኢትዮጵያውያን “የተማረ ሰው ወድቆ አይወድቅም” የሚሉትም ሀገር በልጆቿ ብርታት እና ጥንካሬ ልክ እንደምትሠራው ሁሉ ትውልድም ከሀገር ቀድሞ የሚገነባው በትምህርት እንደኾነ ስለሚያውቁ ነበር፡፡
ድህነት እና ጦርነት ብዙም በማይነጥፍበት የኢትዮጵያ ሰማይ ስር ትምህርትን፣ ተማሪን፣ አስተማሪን እና ትምህርት ቤቶችን ከጥቃት እና ከጉዳት የሚታደገው የሀገሬው ሕዝብ ነባር ባሕል ቀሪውን ዓለም የሚያስተምር እሴት ነበር፡፡
“እንኳን ሰው ዛፍ ያስጥላል” እንዲሉ ኢትዮጵያውያን በብሒላቸው ትናንት ከትናንት ወዲያ በሃይማኖት ተቋማት እና በትምህርት ቤቶች ጥላ ስር ፍፁም ሰላም የነበረው ለትምህርት እና ዕውቀት፤ ለሃይማኖት እና ዕውነት ከነበራቸው የተለየ ቦታ በመነጨ ነው፡፡
ዛሬ ግን ትናንትን አልኾነም፡፡ በሀገሬው ሕዝብ ዘንድ የሚፈሩ፣ የሚታፈሩ እና የሚከበሩ የትምህርት ተቋማት በውኃ ቀጠነ በሚፈጠር ግጭት ሰለባ እየኾኑ መጥተዋል፡፡
የሩቁን ትተን የቅርቡን ብናነሳ እንኳን ኢሕአፓ የተማረ ትውልድ አሳጥቶን ካልኾነ በቀር ትምህርትን እና ትምህርት ቤቶችን ግን የጥቃት ሰለባ አላደረገም ነበር የሚሉት የቀድሞው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ አሁን አሁን የሚስተዋሉ ልምምዶች ከሕዝብ እሴት እና ሞራል እየወጡ ነው ይላሉ፡፡
ግጭት የዓለም ሀገራት ሁሉ ክስተት እንደነበር በታሪክ አይተናል ያሉት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ትምህርትን ከግጭት እና ጦርነት ሰለባነት ለመጠበቅ ግን ሁለት መሠረታዊ መነሻዎች አሉ ነው የሚሉት።
የመጀመሪያው የትምህርት ተቋማት ከየትኛውም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ውግንና ነጻ እና ገለልተኛ ተቋማት መኾናቸው ነው፡፡
ሌላው ግን በየትኛውም ሀገር የጦርነት ታሪክ ውስጥ ከግጭት ማግስት ወጭ ቀሪ ሲሰላ የሚቀሩት ሕዝብ እና ሀገር በመኾናቸው ለሀገራት መጻዒ እጣ ፋንታ ሲባል ትምህርት ቤቶች ከጥቃት ሰለባነት ነጻ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው ግጭት እና የሰላም እጦት በትምህርት ሥርዓቱ ላይ አደጋ መደቀኑ ለሁሉም ግልጽ ነው ያሉት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ “ሀገር የምትገነባው በሰው ነው፤ ሰውን የሚሠራው ደግሞ ትምህርት ነው፤ እናም ለሀገር እና ለትውልድ ሲባል ትምህርት ላይ የሚቃጡ ጥቃቶች ሊቆሙ ይገባል” ነው ያሉት፡፡
ትምህርትን ከጥቃት ነጻ አድርጎ ሕልውናውን ለማስቀጠል ደግሞ ከዛሬ የተሻለ ነገ የለም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleአሚኮ ከባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ማዕከል ጋር የበለጠ ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።
Next articleበአካታችነት ምዘና ላይ ጥሩ የፈጸሙትን ማበረታታት እና ድክመት የታየባቸውን ማገዝ ይገባል።