አሚኮ ከባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ማዕከል ጋር የበለጠ ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

6
ባሕር ዳር: ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ማዕከል ጋር በስፖርቱ ዘርፍ የበለጠ ተቀራርቦ እና በጥምረት ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ የአሚኮ ስፖርት ክፍል እና ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዓላማቸው ተመሳሳይ ነው ብለዋል። የክልሉን ስፖርት እና ስፖርተኞች እንቅስቃሴ ማሳደግ እና በክልሉ ሁለንተናዊ የዘርፉ እድገት እንዲመጣ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ሁለቱም ተቋማት የበለጠ ተቀራርበው እና በጋራ በመሥራት በዘርፉ ውጤታማ የኾነ ውጤት ለማስመዝገብ እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል። የዛሬው የስምምነት ፊርማም ይህንን ትብብር ለማላቅ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ስታዲየሙ ደረጃውን ጠብቆ እንዲገነባ እና ከዚህ እንዲደርስ ሲሳተፉ የነበሩ ባለድርሻ አካላት ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ጋዜጠኛ ሙሉቀን አሚኮም በስታዲየሙ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ስቱዲዮ እየገነባ ነው ብለዋል። ይህ ዘመናዊ ስቱዲዮ መገንባቱ የስፖርት ቤተሰቦችን በቅርበት በማግኘት ውጤታማ ዘገባዎችን ለማዘጋጀት ያግዛል ነው ያሉት።
የአሚኮ መሪዎች የተሰጠውን ዕድል እና ኀላፊነት በአግባቡ በመወጣት የስቱዲዮ ግንባታውን በጥራት እና በፍጥነት እያከናወኑ መኾኑንም ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ማዕከል ሥራ አመራር ቦርድ ሠብሣቢ እርዚቅ ኢሳ ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከአሚኮ ጋር ያደረገው ስምምነት በጋራ በመሥራት የስፖርት ዘርፉን ትርጉም ባለው መልኩ ለማሳደግ ይጠቅማል ብለዋል።
ስታዲየሙ የሚጠበቅበትን ሁሉ መመዘኛ አሟልቷል ያሉት ቦርድ ሠብሣቢው አሚኮ የሚገነባው ዘመናዊ ስቱዲዮም የስታዲየሙን ደረጃ ከፍ ከሚያደርጉ እና ተመራጭነቱን ከሚጨምሩ ግብዓቶች ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል።
ስታዲየሙ ስፖርታዊ ውድድሮችን ብቻ ሳይኾን ልዩ ልዩ ክልል አቀፍ እና ሀገራዊ ፌስቲቫሎችንም እንደሚያስተናግድ ገልጸዋል። የአሚኮ ስቱዲዮ ሁነቶችን በቅርበት ለመዘገብ ያስችላል ነው ያሉት።
ዛሬ የተደረገው የሥምምነት ፊርማ በተሻለ ትብብር በመሥራት ጥራት እና ቅልጥፍና ያለው አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአሚኮ እና የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከፍተኛ መሪዎች እና የስፖርት ዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደሴ ዲስትሪክት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ማዕድ አጋራ።
Next articleሀገር የምትገነባው በሰው ነው፤ ሰውን የሚሠራው ደግሞ ትምህርት ነው።