
ደሴ፡ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደሴ ዲስትሪክት የ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ማዕድ አጋርቷል።
አሚኮ ያነጋገራቸው ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደሴ ዲስትሪክት ዳይሬክተር ሰይድ አሊ ባንኩ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሲደግፍ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ዛሬም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ከ200 በላይ ወገኖች ለእያንዳንዳቸው ከ6ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የዘይት እና ዱቄት ድጋፉ ማድረጉን ገልጸዋል።
ለዚህም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉንም ተናግረዋል።
በቀጣይም ይህንን እሴቱን በማጎልበት የወገን ደራሽነቱን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥልም ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተወካይ ትዝታ ወንድሙ ባንኩ ያከናወነው ሰው ተኮር ተግባር አበረታች መኾኑን ተናግረዋል። ሌሎች ተቋማትም መንግሥት ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እያከናወነ ያለውን ጥረት እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ ፦አንተነህ ፀጋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!