የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት የኪነጥበብ ጉዞ ወደ ሩሲያ ሊደረግ ነው።

4
አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከሻኩራ ፕሮዳክሽን ጋር በመኾን በሰጡት መግለጫ ኪን ኢትዮጵያ የማንሰራራት ብስራት የጥበብ ጉዞ ቀደም ሲል ወደ ቻይና መደረጉን እና ኢትዮጵያን በልኳ ማስተዋወቅ የተቻለበት እንደነበር የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ተናግረዋል።
በጉዞው የኢትዮጵያን ቡና፣ ባሕል፣ ሙዚቃ፣ አልባሳት፣ ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች መኾኗን እና ሌሎችንም ሃብቶቿን ለማሳየት እንደቻለችም አብራርተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንደ ሲጂቲኤን፣ ሲሲቲቪ እና ሽንዋን የመሳሰሉ ታላላቅ ሚዲያዎችም የቀጥታ ሽፋን በሰጡበት መድረክ ላይ ኢትዮጵያ መገለጫዎቿን ማስተዋወቅ እንደቻለችም ነው የተናገሩት።
በስፖርት ዲፕሎማሲ እና ልማት ላይም ስኬታማ ውይይቶች እና ትብብሮች ተደርገዋል ብለዋል።
በተጨማሪም በተሠራው ሥራ በርካታ ቻይናውያን ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም እንዲመጡ መግባባቶች ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
ዋናው የጉዞው ዓላማ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር መፍጠር፣ ቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ፍሰትን መጨመር የሚያስችሉ ሥራዎች መሥራት በመኾኑ ይህንን ከታሰበው በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ግንኙነት ለረጅም ዘመናት የቆየ እና የሚያስተሳስሩ እንደ ፑሽኪን የጥበብ ማዕከል ያሉ ተቋማት እና ግለሰቦች ያሏቸው ሀገራት እንደኾኑም ነው ያብራሩት።
ከጳጉሜን አራት ጀምሮ ጉዞ ወደ ሩሲያ ይደረጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በሴንት ፒተርስበርግ እና ሞስኮ ትርዒቶች እንደሚደረጉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን መልክ በቡና፣ በሙዚቃ፣ በአልባሳት እና ቤሎችም የባሕል ጥበባት ለማስተዋወቅ ጥረት እንደሚደረግም አብራርተዋል።
በተለይ በሞስኮ የሚቀርበው ትርዒት ላይ ከ60 በላይ ሀገራት የሚታደሙበት ዓለማቀፋዊ የባሕል እና የጥበብ ትርዒት ስለሚኖር ይህ ቡድኑ ለሚያደርገው ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ጉዞ ትልቅ አጋጣሚ ይኾናል ብለዋል።
ጎን ለጎንም ልዩ ልዩ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች እና ስምምነቶች እንደሚኖሩ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠቆሙት።
የሻኩራ ፕሮዳክሽን ባለቤት እና የቡድኑ መሪ ሙዚቀኛ ካሙዙ ካሳ የቻይናው ጉዞ የተሳካ እንደነበር ገልጸው ለሩሲያው ጉዞ 65 የቡድኑ አባላት ተሳታፊ እንደሚኾኑ እና በሙዚቃ፣ በፋሽን ትርዒት ብሎም በሌሎችም ጉዳዮች ኢትዮጵያን ለማሳየት መዘጋጀታቸውን ነው ያረጋገጡት።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleኀብረት ሥራ ማኀበራት ገበያን በማረጋጋት ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ ነው።
Next article“በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አይተናል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ