በጸጥታ ምክኒያት አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እየተመለሱ ነው።

6
ባሕር ዳር: ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር አሥተዳደር ዞን የሚገኙ የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ልጆቻቸውን እያስመዘገቡ ነው።
ተማሪዎችም ትምህርት አቋርጠው በመክረማቸው ተቆጭተው አሁን ላይ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ምዝገባ እየተካሄደ በመኾኑ ተደስተዋል።
አምላኩ ወርቁ በምዕራብ ጎንደር አሥተዳድር ዞን በቋራ ወረዳ የገለጉ ከተማ ነዋሪ እና የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው።
ይሁንና በቀዬው በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት የሚወደውን ትምህርት አቋርጦ በመክረሙ ተጎድቻለሁ አለን።
“ትምህርቴን አቋርጨም ውሎየ ሁሉ የነበረው ከብት መጠበቅ ነበር የሚለው ተማሪው ባለመማሬም ከዓለም እንደተለየሁ ተሰምቶኛል” ብሏል።
ትምህርቴን በአግባቡ ተምሬም ዶክተር እኾናለሁ ስል ትምህርቴን እንዳቋርጥ በመገደዴ አዝኛለሁ ሲል ያብራራል። እንደ’ኔ ተስፋቸውን በትምህርት ላይ ያደረጉ ታዳጊዎችም ብዙ ናቸው ብሏል።
…ዘንድሮ ግን ያ ሁሉ ሐዘን በተስፋ ሊቀየር ጎሕ የቀደደ እየመሰለን ነው የሚለው ተማሪው ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ለመማር በመመዝገቡ እንደተደሰተም ጠቁሟል።
ትምህርት አቋርጠው የከረሙትን ጓደኞቹንም የምዝገባው ዕለት በማግኘቱ ደስታውን እጥፍ አድርጎታል።
ተማሪ አምላኩ ሁለት ዓመት ሙሉ ትምህርት አቋርጦ ባይከርም ኑሮ ዘንድሮ ዩኒቨርሲቲ እንደሚገባ ሲያስታውስ ቢከፋም “ቀሪው ዘመን ሰላም ከኾነ ይደረሳል”የሚል ብሩሕ ተስፋ መሰነቁን ነው የነገረን።
ልጆች ተምረው ትልቅ የመኾን፣ ሀገር ወገን የመጥቀም ራዕይ እና ተስፋ አላቸው።
ይህ ምኞት እና ብሩሕ ተስፋ ወደ ሚጨበጥ ዕውነት የሚቀየረው ደግሞ በተዓምር ሳይኾን በትምህርት ብቻ ነው።
ለዚህ ደግሞ ኀብረተሰቡ ድርብ ኀላፊነት አለበት። ልጆችን ተንከባክቦ የማሳደግ እና የማስተማር።
የአማራ ክልል በገጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ አካባቢዎች ተዘግተው ከርመዋል።
በዚህም በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ነው የቆዩት።
ልጆች ትምህርት በማቋረጣቸው ደግሞ ለተለያዩ ችግሮች እንደተጋለጡ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።
የኾነው ኾኖ አሁን ላይ የክልሉ ሰላም በመመለሱ በምዕራብ ጎንደር አሥተዳደር ዞን ቋራ ወረዳ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ እየተካሄደ መኾኑን በወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት የዕቅድ ዝግጅት ባለሙያ አምባቸው ፈቃዱ ለአሚኮ ተናግረዋል።
ባለሙያው እንዳሉት ትምህርት ቤቶች የተከፈቱት ለኀብረተሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ከተከናወነ በኋላ ነው።
ማኀበረሰቡም በነበረው ውይይት “በልጆቻችን ላይ ጦርነት ከሚያስከትለው ጉዳት ባልተናነሰ በትምህርት መቋረጥ የሚመጣው ጉዳት የከፋ ነው” የሚል ቀናዒ አስተሳሰብን በመላበስ ልጆችን ትምህርት ቤት ድረስ እያመጣ ነው ብለዋል።
ይህ ዘገባ አስከ ተጠናከረበት ዕለት ድረስም 2ሺህ 200 ትምህርት አቋርጠው የቆዩ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ነው አቶ አምባቸው የተናገሩት።
በወረዳው 77 የአንደኛ ደረጃ እንዲኹም ሦሥት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙም ነው ባለሙያው የጠቆሙት።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ የዕቅድ ዝግጅት ቡድን መሪ አሚር አሊ በበኩላቸው ለ2018 የትምህርት ዘመን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናዎናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ 146ሺህ መደበኛ ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ ምዝገባው መቀጠሉን ነው ቡድን መሪው የገለጹት።
9 ሺህ ጎልማሶችን እና የልዩ ፍላጉት ተማሪዎችንም ለማስተማር ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
ይህን ዕቅድ ዕውን ለማድረግም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እና በንቅናቄ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በዞኑ አራት ወረዳዎች እና አንድ ከተማ አሥተዳደር ይገኛል ያሉት ቡድን መሪው በሁሉም ወረዳዎች እና በከተማ አሥተዳደሩ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል።
ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር ይፈልጋሉ፤ ተማሪዎችም የመማር ጉጉት አላቸው ነው ያሉት ቡድን መሪው።
ይህ ሃሳብ በተደጋጋሚ በተደረጉ የንቅናቄ መድረኮች ላይ መንጸባረቁንም ተናግረዋል።
ትምህርት ተቋርጦ በመቆየቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ደርሷል ያሉት ቡድን መሪው አካባቢው ከጎረቤት ሀገር ጋር የሚዋሰን በመኾኑ በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወደ ውጭ ሀገር ለመሰደድ ሲሞክሩ ህይወታቸውን ያጡ መኖራቸውን አንስተዋል።
ትምህርት ቢኖር ኑሮ ልጆች ተረጋግተው መማርም መኖርም ይችላሉ የሚል ተስፋ እና ቁጭት ኀብረተሰቡ ማሳደሩን ነው ቡድን መሪው የተናገሩት። ስለዚህ ኀብረተሰቡ በአሁኑ ሰዓት ልጆቹን እያስመዘገበ ነው ብለዋል።
ወላጆች እና አሳዳጊዎች ልጀችን ትምህርት ቤት ከማስመዝገብ ባለፈ የተጎዱ እና የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገን የአቅማቸውን አስተዋጽዖ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
ይሁን እንጅ በዞኑ በርካታ ትምህርት ቤቶች በመጎዳታቸው እና በመውደማቸው መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና ግብረ ሠናዮች ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት እስከ መጠገን፣ ግብዓት እና ቴክኖሎጂ እስከ ማሟላት እንዲደግፏቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
ማንኛውም አካል ትምህርትን በማቋረጥ በልጆቻችን፣ በትውልዱ እና በዜጋው ላይ የሚቀልድበት ጊዜ ማክተም አለበት ነው ያሉት።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በትምህርት ዘመኑ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱን መግለጻቸው ይታወሳል። ለዚህም በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።
ቢሮ ኀላፊዋ በትምህርት ጉዳይ ላይ አኹን የተፈጠረው የማኅበረሰቡ ቁጭት፣ የአጋር አካላት ድጋፍ እና በየደረጃው ያለው ቅድመ ዝግጅት የታቀደውን ውጤት ለማሳካት አቅም ይኾናልም ብለዋል።
የዚህ ዓመት የመማር ማስተማር ሥራም መስከረም 05/2018 ዓ.ም ይጀምራል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“የኢፌዴሪ የጸጥታ ተቋማት ዋነኛው ተልዕኮ ሰላምን በመላ ሀገሪቱ ማጽናት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ በባሕር ዳር አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።