የስኳር በሽታ እና አሳሳቢነቱ!

4
ባሕር ዳር: ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎችን በከፍተኛ ኹኔታ ለሞት እየዳረጉ እንደኾነ የዘርፉ ባለሙያወች ይገልጻሉ።
የልብ ሕመም፣ የደም ግፊት፣ የኩላሊት ሕመም፣ ስትሮክ፣ ካንሰር እና የስኳር ሕመም በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው።
በዛሬው ዘገባ ታድያ በስኳር በሽታ ላይ ትኩረታችን አድርገናል።
አሁን ላይ በዓለም ላይ 827 ሚሊዮን የሚኾኑ ሰዎች ከስኳር ጋር ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። በሽታው የኢትዮጵያም የማኅበረሰብ ችግር እየኾነ የመጣ ሲኾን ከ1 ነጥብ 9 እስከ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች ከስኳር ጋር ይኖራሉ ተብሎ ይታሰባል።
ከዚህ ውስጥ አስር በመቶ የሚኾኑት አይነት አንድ የስኳር ታማሚዎች ሲኾኑ 90 በመቶ ደግሞ አይነት ሁለት ሕሙማን ሊኾኑ እንደሚችሉ መረጃዎች ያሳያሉ።
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ እንደነገሩን በስኳር በሽታ በመጠቃታቸው ለዓመታት መድኃኒት እየወሰዱ ይገኛሉ።
ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከስኳር ሕመሙ በተጨማሪ ለልብ ሕመም፣ ለደም ግፊት እና ለኩላሊት በሽታ በቀላሉ እንደተጋለጡም ባለታሪካችን ነግረውናል።
አኹን የኩላሊት እጥበት ጀምረው በከፍተኛ የጤና ችግር ላይ እንደሚገኙ ገልጸውልናል፡፡ ለረጅም ጊዜ ጫት ይቅሙ፣ አልኮል እና ትምባሆ ይጠቀሙ ስለነበር ለተደራራቢ በሽታዎች መጋለጥ እንደምክንያት መኾኑን አንስተዋል። ማንኛውም ሰው ከሱስ ራሱን በማራቅ ጤንነቱን ሊጠብቅ እንደሚገባም መክረዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ ዶክተር ግርማ ደርሶ የስኳር በሽታ በደም ውስጥ ከመጠን በላይ የኾነ ግሉኮስ ሲኖር የሚፈጠር ነው ብለዋል። በሽታው የዕድሜ ልክ የጤና ችግርም ሊኾን እንደሚችልም ተናግረዋል።
መንሥኤው ደግሞ በተፈጥሮ ከጣፊያ የሚመነጭ ኢንሱሊን የተባለ ኾርሞን በጣም ሲያንስ፣ እጥረት ሲያጋጥም ወይንም በቂ የኾነ ኾርሞን ኖሮ የሚገባውን ሥራ መሥራት ሳይችል ሲቀር የሚከሰት የጤና ችግር ነው ብለዋል።
የስኳር በሽታ ዓይነቶችን በተመለከተ ዶክተር ግርማ ደርሶ አራት አይነት የስኳር በሽታ ቢኖሩም ዋና ዋናዎቹ ሁለት አይነት ናቸው ይላሉ።
አንደኛው ዓይነት አንድ የሚባለው ሲኾን በአብዛኛው እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች በኾኑ ላይ የሚከሰት ነው። አይነት አንድ የስኳር ሕመም ኢንሱሊን የሚመረትበትን የአካል ክፍል በማጥቃት በድንገት የሚከሰት በመኾኑ መከላከል እንደማይቻል ነው የገለጹት።
ሁለተኛው ደግሞ ዓይነት ሁለት የሚባለው የስኳር በሽታ ነው። በአብዛኛው ከ40 ዓመት በላይ የዕድሜ ክልል ባሉት ግለሰቦች ላይ የሚከሰት በሽታ ነው ይላሉ። ይኹን እንጅ አሁን ላይ አይነት ሁለት የሚባለው የስኳር በሽታ በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ጭምር እየተከሰተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የአኗኗር ዘይቤ፣ የአመጋገብ ኹኔታ ማለትም ቅባት የበዛባቸውን ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ፣ ስኳር የበዛባቸው እና ያለቀላቸው ምግቦች እና ለስላሳ መጠጦችን ማዘውተር፣ አልኮል አብዝቶ መጠቀም፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ ውፍረት የሚሉትን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
የተጠቀሱትን መንስኤዎች ላይ ትኩረት ከተደረገ አይነት ሁለት የስኳር በሽታን መከላከል እንደሚቻል ገልጸዋል።
የስኳር በሽታ ምልክቶችን በተመለከተ ደግሞ በጤና ተቋማት በየጊዜው ምርመራ ካልተደረገ በስተቀር በሽታው ቶሎ ምልክት እንደማያሳይ ባለሙያው ጠቁመዋል።
በተለይም ደግሞ አይነት ሁለት የስኳር በሽታ ምልክት ሳያሳይ ከአስር ዓመት በላይ አብሮ ሊኖር ይችላል ነው ያሉት። ከረጅም ጊዜ በኋላ ደግሞ የሚከተሉትን ምልክቶች ያሳያል።
የረሃብ ስሜት፣ ከተለመደው በላይ መመገብ፣ ከፍተኛ የውኃ ጥም፣ ብዙ ጊዜ መሽናት (በቀን እና በሌሊት ቶሎ ቶሎ የሚመጣ ሽንት) ምልክቶችን ያሳያል ብለዋል።
ድንገተኛ የኾነ የክብደት መቀነስ፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት፣ ተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን፣ ቁስል በቶሎ ያለመዳን፣ የቆዳ መጥቆር፣ የእጅ እና እግር መደንዘዝ ወዘተ ምልክቶች ናቸው ብለዋል። መጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርስ ደግሞ ዐይን፣ ነርቭ፣ ጭንቅላት፣ ልብ፣ ነርቨ፣ ኩላሊትን ያጠቃል ነው ያሉት።
የስኳር በሽታ ሕክምና እንደ ስኳር በሽታው ዓይነት እና እንደ ታማሚው ሊለያይ ይችላል ብለዋል። የስኳር ታማሚ በሐኪም የታዘዘለትን መድኃኒት (በተለይ ኢንሱሊን) በየጊዜው ተከታትሎ መውሰድ ይጠበቅበታል። ከዚያም ባለፈ በሽታው እንዳይጠና አመጋገብን ማስተካከል እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል ይላሉ።
በዓመት አንድ ጊዜ ስኳር እና ተዛማጅ በሽታዎችን ምርመራ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleመውሊድ አብሮነት እና መደጋገፍን የሚጠይቅ የአንድነት በዓል ነው።
Next article“የኢፌዴሪ የጸጥታ ተቋማት ዋነኛው ተልዕኮ ሰላምን በመላ ሀገሪቱ ማጽናት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)