
ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ)1 ሺህ 500ኛው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ አንዋር መስጅድ ተከብሯል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዑለማዎች የመድረሳ እና የዳዕዋ ዘርፍ አስተባባሪ ሼኽ ሙሐመድ ሱሌማን የመውሊድ በዓል የነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ሱና በመከተል በፍቅር እና በአብሮነት የሚከበር ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ነው ብለዋል።
በዓሉን ሕዝበ ሙስሊሙ እርስ በእርስ በመረዳዳት እና በመከባበር ሊያከብረው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የመውሊድ በዓል በሃይማኖታዊ አስተምህሮው መሰረት በዳዕዋ፣ በሰጊድ እና በሌሎችም ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች እንደሚከበር የተናገሩት ደግሞ ዑስታዝ ሰዒድ ሐሰን ናቸው።
ሕዝበ ሙስሊሙ በቻለው አቅም የተለያዩ በጎ ተግባራት በማከናዎን የሚያከብረው እና የነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) እዝነት የሚሻበት በዓል መኾኑን ተናግረዋል።
የደባርቅ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ካሳ እስማዔል መውሊድ ከበዓል ዝግጅቱ ጀምሮ አብሮነት እና መደጋገፍን የሚጠይቅ የአንድነት በዓል ነው ብለዋል።
ከበዓሉ በኋላም የአብሮነት እና የመደጋገፍ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በበዓሉ አከባበር የተገኙት የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ክንዴ ተፈራ ሕዝበ ሙስሊሙ የመተሳሰብ እና የአብሮነት ባሕሉን በማሳደግ ሀገራዊ ተሳትፎውን ሊያጎለብት ይገባል ብለዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎችም በዓሉ በመተሳሰብ እና በአብሮነት ተከብሮ መዋሉ ደስታን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
በዓሉ ከሃይማኖታዊ ፋይዳው በተጨማሪ ሀገራዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳው የጎላ ነው ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን