ሕዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር የነብዩ መሐመድ ( ሰ.ዐ.ወ) መልካምነትን በመግለጽ ሊኾን ይገባል።

5
ሁመራ፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር የነብዩ መሐመድን ( ሰ.ዐ.ወ) ምግባራት በማስቀጠል መኾን እንደሚገባ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሸሪያ ፍርድ ቤት አሳስቧል።
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ለ1 ሺህ 500ኛ ጊዜ የሚከበረው የነብዩ መሐመድ ( ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል በሁመራ ከተማ አጢቅ መስጊድ በድምቀት ተከብሯል።
ሕዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር የነብዩን መልካምነት በመግለጽ ሊኾን እንደሚገባ የተናገሩት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሸሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ ሼኽ ዑመር መሐመድ ናቸው፡፡
ነብዩ መሐመድ ( ሰ.ዐ.ወ) የተላኩት ለእዝነት እና ለርኅራሄ በመኾኑ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በዓሉን ሲያከብር አቅመ ደካሞችን በማሰብ እና በመፍቀድ ሊኾን እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
ነብዩ መሐመድ ( ሰ.ዐ.ወ) ትኩረታቸው ወጣቱ ላይ ነበር ያሉት ሼኽ ዑመር የእሳቸውን ፈለግ በመከተል ሕዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓሉን ሲያከበር ለሀገር ሰላም እና አንድነት በመጸለይ እና አስተምህሮዎችን በመተግበር ሊኾን ይገባል ብለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙ የሃይማኖቱ ተከታዮችም በዓሉን በአንድ ላይ በመሆን ማዕድ በመጋራት እነዳከበሩት ገልጸዋል። በዓሉን ነብዩ መሐመድን ( ሰ.ዐ.ወ) በማሰብ እና የእሳቸውን ትዕዛዛት በመፈፀም ማክበር እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ በዓሉ ፍቅርና ሰላም የሚሰበክበት መኾኑንም ጠቁመዋል።
በዓሉ በቂራት፣ በዱአ እና በመንዙማ የሃይማኖቱ ሥርዓቶች ተከብሯል። ሕዝበ ሙስሊሙ የነብዩ መሐመድን ( ሰ.ዐ.ወ) ምግባራት ማስቀጠል እንደሚገባውም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleስብዕናው የተገነባ ትውልድ ሀገር ይገነባል።
Next articleመውሊድ አብሮነት እና መደጋገፍን የሚጠይቅ የአንድነት በዓል ነው።