ስብዕናው የተገነባ ትውልድ ሀገር ይገነባል።

7
ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የዓለም ወጣቶች ቀን የማጠቃለያ ዝግጅት ተካሂዷል። ዝግጅቱ “የተደመረ የወጣቶች አቅም ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተካሄደው።
የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ እያበቁ ሥራ ፈጣሪ እየኾኑ መኾናቸውን ገልጸዋል። በሀገር አቀፍ የወጣቶች የበጎ አድራጎት ሥራ መሳተፋቸውን የተናገሩት ወጣቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራቸውን ማሳረፋቸውን፣ የአረጋውያን ቤት ማደሳቸውን፣ የአእምሮ ሕሙማንን መንከባከባቸውን እና ለሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን መፈጸማቸውን ነው የገለጹት። ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራቸው ባሻገር የኢትዮጵያውያንን ፍቅርን እና አብሮነትን ማጎልበታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያውያንን የፍቅር እና የአንድነት አኗኗር ማየታቸውንም አንስተዋል።
የተሻለ የሥራ እድል ፈጠራዎች ላይ ልምድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል። በጎነት ለክፉ ቀን ስንቅ ነው ያሉት ወጣቶቹ በአካል ያየናት ኢትዮጵያ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ያለችው ኢትዮጵያ የተለያዩ መኾናቸውን ተገንዝበናል ነው ያሉት። ወጣቶች በመላው ኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ በመሥራት ትክክለኛዋን ኢትዮጵያ ማወቅ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የወጣቶች ጉዳይ አማካሪ ብርሃኑ አበበ ወጣቶች በመደራጀት እንዲንቀሳቀሱ መብት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። ወጣቶች ሲደራጁ አቅማቸውን ለማጎልበት፣ ለማኅበረሰብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
የመሪነት ልምድን እንዲለማመዱ፣ በማኅበረሰብ መካከል ትስስር እንዲጠናከር እንደሚያደርጋቸውም አመላክተዋል። ወጣቶች ችግሮችን በመቋቋም የልማት ተጠቃሚ መኾን እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።
በአማራ ክልል የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የሥራ እድል ፈጠራ ዳይሬክተር ፍቅረማርያም የኔአባት ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ አማራጮች እንዳሉም አንስተዋል።
በክልሉ የሥራ እድል የሚፈጠርባቸው ጸጋዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ወጣቶች እድሎችን በመጠቀም የሥራ እድል ተጠቃሚ መኾን እንደሚገባቸውም አመላክተዋል። ወጣቶች የሚመቻችላቸውን ብድር እና የሥራ ቦታ በአግባቡ መጠቀም ከቻሉ መለወጥ እንደሚችሉም ገልጸዋል።
ወጣቶች ለሥራ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው እና እውቀትን መፈለግ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኀላፊ የቻለ ይግዛው ወጣቶች ማኅበራዊ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ መኾናቸውን ገልጸዋል። ለወጣቶች ቴክኖሎጂ ሲጨመር በቀላሉ የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው፣ በቀላሉ በዓለም ካለው ማኅበረሰብ ጋር እንዲገናኙ ያደርጋል ነው ያሉት።
ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሥራ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥራ እድል ፈጠራ ትኩረት እንደተሰጠውም ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂ ዓለምን የሚቀይር ገዢ ኾኗል ያሉት ምክትል ኀላፊው የቴክኖሎጂን ጸጋ በአዎንታዊ መልኩ መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል። የቴክኖሎጂን ልክ በልኩ መረዳት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል። ቴክኖሎጂን በአግባቡ ለመጠቀም የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትን ማሟላት እንደሚገባም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ወጣቶች የፈጠራ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የወጣቶችን የፈጠራ ሃሳብ በገንዘብ መደገፍ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ምቹ እድል እንደፈጠረም ተናግረዋል።
ራስን ለማይቀረው የቴክኖሎጂ ዘመን ማዘጋጀት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ ስብዕናው የተገነባ ወጣት የተደመረ አቅም የመፍጠር እድሉ ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። የወጣቶች ስብዕና በብዙ መልኩ ይገነባል ያሉት ኀላፊው ስብዕናው የተገነባ ትውልድ ደግሞ ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ጠቃሚ ባሕሎቻችን እና እሴቶቻችን እንዳይሸረሸሩ በአግባቡ መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት። የባሕል፣ የማንነት እና የእሴት መበረዝ እንዳይመጣ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። የቴክኖሎጂ መስፋፋትን በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ በባሕል፣ በእሴት እና በማንነት ግንባታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ተናግረዋል።
በ25 ዓመታቱ የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት እቅድ ለእሴት ግንባታ ትኩረት እንደተሰጠም ገልጸዋል። የስብዕና መጓደል ሲኖር ለሀገር እድገት አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።
ወጣቶች ሀገራዊ ማንነት፣ ስብዕና፣ ባሕል እና እሴትን መጠበቅ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። የኢትዮጵያን የአንድነት፣ የአይደፈሬነት፣ የጀግንነት ማንነት ማስጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል። በትልቅ ማንነት የተገነባን ኾነን ሳለ እርስ በእርስ መጋጨት፣ አለመስማማት፣ ተማሪዎች እንዳይማሩ ማድረግ ለማንነታችን አይመጥንም ነው ያሉት።
ወጣቶች ለራሳቸው፣ ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው ታማኝ እንዲኾኑም አስገንዝበዋል። በውጭ ባሕል፣ ወግ እና እሴት መሸነፍ እንደማይገባ እና የራስን እሴት፣ ባሕል እና ማንነት መጠበቅ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል። ወጣቶች ምንም ቢኖራቸው ስብዕና ከሌላቸው ውጤታማ መኾን አይችሉም ነው ያሉት። የእድገትና የልማት መቋጫው ስብዕና ነው ብለዋል።
ወጣቶች አልችልም የሚልን አመለካከት ማስወገድ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። ወጣቶች አእምሯቸውን በዕውቀት፣ አካላቸውን ደግሞ በስፖርት መገንባት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ራሳቸውን ብቁ ካደረጉ ከራሳቸው አልፈው ሀገርንም መጥቀም እንደሚችሉ ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበሥራና ሥልጠና ቢሮ በለሙ ሲስተሞችም ለ300 ሺህ ሥራ ፈላጊዎች ሥራ ተፈጥሯል።
Next articleሕዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር የነብዩ መሐመድ ( ሰ.ዐ.ወ) መልካምነትን በመግለጽ ሊኾን ይገባል።