
ጎንደር: ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች በጠዳ የሥልጠና ማዕከል ሲወስዱት የነበረውን ሥልጠና አጠናቅቀው ነው ዛሬ የተመረቁት።
በጠዳ የሥልጠና ማዕከል ሲሠለጥኑ የቆዩ ሠልጣኞች ለሰላም መስፈን የነበራቸውን ቁርጠኝነት በሥልጠናው ወቅት ማሳየታቸውን በማጠናቀቂያ መርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ገልጸዋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በሀገሪቱ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ወገኖችን ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም አቶ በሪሁን አንስተዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ያነሱት አቶ በሪሁን መንግሥቱ ለሰላም መስፈን ሁሉም ሊተባበር ይገባል ብለዋል።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን በሀገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የኮሚሽኑ የጠዳ ማዕከል አሥተባባሪ አቶ ግዛቸው መኩሪያ ተናግረዋል። ሰላም እና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛልም ብለዋል።
በስልጠናው የተገኙ ሀሳቦችን በግብዓትነት በመጠቀም መንግሥትም፣ ኮሚሽኑም ይጠቀምባቸዋልም ብለዋል አቶ ግዛቸው። በጫካ የሚገኙ ወገኖች ለሰላም እጃቸውን እንዲዘረጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ሰልጣኞች በበኩላቸው በሥልጠና ማዕከሉ ቆይታቸው በተሰጡ ሥልጠናዎች የአመለካከት ለውጥ ማምጣታቸውን አንስተዋል። ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ሰላም እንዲሰፍን የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ደስታ ካሳ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን