“በምርት ዘመኑ ምርታማነትን በሄክታር 35 ኩንታል ለማድረስ እየተሠራ ይገኛል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

3
ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ 2017 ዓ.ም የግብርና ሥራ እቅድ አፈጻጸም እና በ2018 ዓ.ም እቅድ ላይ ከክልሉ እና ከዞን የግብርና ኀላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ የተከሰተውን የሰላም ችግር ከመቅረፍ ጎን ለጎን ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ለውጦችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ በ2017 የምርት ዘመን ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሥራቱን ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል።
ከ170 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱን ኀላፊው ገልጸዋል። በሄክታርም ከ28 ኩንታል ወደ 32 ኩንታል ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ከ7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በወቅቱ በመሠራጨቱ እና አዲስ የኤክስቴንሽን አደረጃጀት ወደ ልማት መግባት በመቻሉ የተገኘ ውጤት መኾኑን ገልጸዋል። ለምርት እድገቱ በግብርና ዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።
በ2017/18 የምርት ዘመንም ከ25 ዓመት አሻጋሪ እቅድ የተቀዳ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። በግብርናው ዘርፍ 8 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ለማስመዝገብም ግብ ተቀምጦለታል።
እቅዱን ለማሳካት እስከ አሁን 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተሠራጭቷል። ከዚህም ባለፈ ለሜካናይዜሽን ሥራ ትኩረት ተሠጥቷል።
አሲዳማ አፈርን በኖራ ማከም፣ ጥቁር አፈርን አጠንፍፎ መጠቀም ሥራዎች ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው።
የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር ውኃ በመጠቀም መስኖን ማልማት ሌላኛው ትኩረት መኾኑን ገልጸዋል።
ምርታማነቱንም በሄክታር አሁን ካለበት ከ32 ኩንታል ወደ 35 ኩንታል ለማድረስ ግብ ተቀምጦለታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየመውሊድ በዓል ሲከበር በአብሮነት፣ የተቸገሩትን በማገዝ እና በመረዳዳት ሊኾን ይገባል።
Next articleየመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ እና በጠዳ የሥልጠና ማዕከል የቆዩ ታጣቂዎች ሥልጠናቸውን አጠናቀቁ።