
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ከዞን እና ከተማ አሥተዳደረ የገንዘብ መምሪያዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና 2018 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር) የ2018 በጀት ዓመት እንደ ክልል አዲስ የስትራቴጂክ ፕላን ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ የሚገባበት ነው ብለዋል።
እስካሁን ወጭን መሠረት ተደርጎ የሚዘጋጅ በጀት እንደነበር የተናገሩት ቢሮ ኀላፊው በ2018 በጀት ዓመት ወደ ፕሮጀክት በጀት ዝግጅት ሽግግር ይደረጋል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በርካታ ነገሮች ይሻሻላሉ ያሉት ዶክተር ጥላሁን በተለይ የግዥ ዓውዶች እና መመሪያዎች ተሻሽለው ሥራ ላይ ይውላሉ ነው ያሉት።
ዶክተር ጥላሁን የ2018 በጀት ዓመት የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ዘዴ ሽግግር የሚደረግበት ወቅትም ይኾናል ነው ያሉት።
በፌዴራል ደረጃ የመንግሥት የፋይናንስ አዋጅ ወጥቶ ሥራ ላይ መዋሉን ያስታወሱት ቢሮ ኀላፊው እንደ ክልልም የመንግሥት የፋይናንስ አዋጅን ከክልሉ ነባራዊ ኹኔታ ጋር ሊጣጣም በሚችል መልኩ በማሻሻል በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ አዳዲስ ነገሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን