የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የ25 ዓመቱን ስትራቴጂክ ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታወቀ።

2
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ቢሮው በክልሉ ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችለውን የ25 ዓመት የፍኖተ ካርታ እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን የገለጹት አቶ ብርሃኑ በ2017 በጀት ዓመት የሕግ ማሻሻያ እና አዲስ ሕጎችን የማዘጋጀት ሥራዎች እንደተከናወኑ አንስተዋል።
ከእነዚህም መካከል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ፣ የጠበቆች አሥተዳደር አዋጅ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
የፍትሕ ሥርዓቱ ፈጣን እና ውጤታማ እንዲኾን ለማስቻልም፦
👉 ወንጀል እና የፍታብሔር መዝገቦችን የመወሰን ቅልጥፍናን ማሳደግ
👉 በወንጀል የተመዘበረ የመንግሥት ሃብት ማስመለስ
👉 የቀበሌ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞችን አቅም ማሳደግ
👉 ለወንጀል ጠቋሚዎች እና ምሥክሮች ሕጋዊ ከለላ መስጠት እና የተጠናከረ የሕግ ግንዛቤ የመስጠት ሥራዎች ተከናውነዋል።
አሁን ላይ ቢሮው የ2018 በጀት ዓመት ዕቅዱን በማዘጋጀት ወደ ተግባር ለመግባት መዘጋጀቱን የገለጹት ኀላፊው ዕቅዱ 10 ስትራቴጂክ ጉዳዮችን፣ 4 የትኩረት መስኮችን እና 14 ግቦችን የያዘ ነው ብለዋል።
ይህ ዕቅድ የክልሉን የ25 ዓመታት ፍኖተ ካርታ እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድን የሚያንጸባርቅ እና አጠቃላይ የክልሉን ዕቅድ የሚያሟላ መኾኑም ተጠቁሟል።
የፍትሕ ቢሮው በቀጣይ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች፦
👉ቴክኖሎጂን መጠቀም
👉ታማኝ የፍትሕ ሥርዓት መገንባት እና ሕግ አክባሪ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደኾነ አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል።
የቢሮው የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ሲኾን የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በመድረኩ ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከዞንና ከተማ አሥተዳደር ኅላፊዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።
Next articleባለፈው ዓመት በክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል።