በሰላም እጦት አገልግሎቱን አቁሞ የነበረው የጤና ተቋም አሁን ላይ ህይወትን እየታደገ ነው።

2
ደብረብርሃን፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኤፍራታ እና ግድም ወረዳ የጀውሃ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረ ግጭት እና በሰሜኑ ጦርነት ሙሉ በሙሉ ውድመት ደርሶበት ቆይቷል።
የጤና አጠባበቅ ጣቢያው አሁን ላይ ወደ አገልግሎት በመመለስ ለኅብረተሰቡ ግልጋሎት እየሰጠም ይገኛል።
በጤና አጠባበቅ ጣቢያው አሚኮ ያገኛቸው ወይዘሮ አላዩ ሲራጅ ጤና ጣቢያው አገልግሎት ባቆመባቸው ጊዜያት ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው እንደነበር ተናግረዋል።
ሴት ልጃቸው ታማባቸው ወደ ሸዋሮቢት ይዘው በመሄድ ለ12 ቀናት በሕክምና ላይ እንደቆዩ ያስታወሱት ወይዘሮ አላዩ በቆይታቸው ለከፍተኛ ወጭ እና እንግልት ስለመዳረጋቸውም ገልጸዋል።
አሁን ላይ ግን አከባቢያቸው ሰላም ኾኖ ጤና ጣቢያውም ሥራ በመጀመሩ በቀያቸው መታከም በመቻላቸው ደስታቸውን ተናግረዋል።
የጀውሃ ቀበሌ ዋና አሥተዳዳሪ ሹሙ ባሼ ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ የቀበሌው እና የአካባቢው ነፍሰ ጡር እናቶች እና ህሙማን በሕክምና እጦት ለሕልፈተ ሕይዎት ሲዳረጉ መቆየታቸውን አብራርተዋል።
ዛሬ ላይ የአካባቢው ሰላም በመረጋገጡ እና የጤና አጠባበቅ ጣቢያው አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ከቀበሌው ነዋሪዎች በተጨማሪ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና ከአፋር ክልል አጎራባች ቀበሌ ነዋሪዎችም ተጠቃሚ እየኾኑ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
የጤና አጠባበቅ ጣቢያው ኀላፊ ታደሰ አጥላው ተቋሙ 25 ሺህ ለሚኾኑ የጀውሃ ቀበሌ እና የአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ እንደኾነ ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ በደረሰበት ውድመት ምክንያት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን ተናግረዋል።
ተቋሙ መልሶ ግንባታ ከተደረገለት በኋላ ወደ ሥራ ስለመመለሱም ነው አቶ ታደሰ የተናገሩት።
የኤፍራታ እና ግድም ወረዳ አሥተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ውብርሰት አሰፋው ከክልሉ ጤና ቢሮ በተገኘ የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እና ከከተማ አሥተዳደሩ 2ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ ጤና አጠባበቅ ጣቢያውን መልሶ በመገንባት ወደ ሥራ ማስገባት ስለመቻሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶችን ከአጋር አካላት በማሠባሠብ አገልግሎቱን ለማስጀመር እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ምላሽ መስጠት ስለመቻሉ አብራርተዋል።
ተቋሙ ለበርካታ የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ አገልግሎት የሚሰጥ በመኾኑም አሁንም ተጨማሪ የሕክምና መሳሪያዎች እና የመድኃኒት አቅርቦት ያስፈልገዋል ያሉት ኀላፊዋ ባለድርሻ እና አጋር አካላት ለጀውሃ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በተግባር ስለኖራችሁ እናመሰግናለን” ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ
Next articleየኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከዞንና ከተማ አሥተዳደር ኅላፊዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።