“ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በተግባር ስለኖራችሁ እናመሰግናለን” ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ

3
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 500ኛው የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓል በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ነው።
በባሕር ዳር ከተማም በሰላም በር መስጅድ የሃይማኖቱ ተከታዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እና የበጎ አድራጎት ድጋፎች እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ የመውሊድ በዓል የሰው ልጆች በእኩልነት፣ እዝነት እና ሰብዓዊነት እንዲኖሩ ያደረገ ነው ብለዋል።
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በአስተምህሯቸው ለሰው ልጅ ሁሉ ሰላም ይኾን ዘንድ ሰርተዋል፤ አስተምረዋል ያሉት ምክትል ከንቲባው ይህ የሰላም፣ የእዝነት፣ እኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና መልካም ሥራዎች ሁሉ በትውልዱ ዘንድ እንዲቀጥሉ የበዓሉ መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የበዓሉ መከበር የነብዩን አስተምህሮ፣ ሃይማኖታዊ ትሩፍቱን እና እሴቱን በትውልዱ ለማስቀጠል ያግዛል ያሉት ምክትል ከንቲባው “ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በተግባር ስለኖራችሁ እናመሰግናለን” ብለዋል።
በበዓሉ ላይ ለ2018 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ ከሰብዓዊነት የመነጨ ነው ያሉት አቶ አስሜ ብርሌ ሕዝበ ሙስሊሙ ለሚፈልገው ድጋፍ ሁሉ ከተማ አሥተዳደሩ እንደሚተባበር ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየነቢዩ መስጅድ ውስጥ የተገጠሙት ቴክኖሎጅዎች።
Next articleበሰላም እጦት አገልግሎቱን አቁሞ የነበረው የጤና ተቋም አሁን ላይ ህይወትን እየታደገ ነው።