የነቢዩ መስጅድ ውስጥ የተገጠሙት ቴክኖሎጅዎች።

5
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሳውዲ አረቢያ ምዕራብ ሂጃዝ ክልል ውስጥ የምትገኘው መዲና ከተማ በእስልምና ሃይማኖት ትልቅ ሃይማኖታዊ ክብር ከሚሰጣቸው ቦታዎች አንዷ ናት።
ከመካ ቀጥሎ በኢስላም ሁለተኛዋ ቅዱስ ከተማ ናት። “የነቢዩ ከተማ” ወይም “የብርሃን ከተማ” በመባልም ትታወቃለች።
አል-መስጅድ አን-ነበዊ በመዲና ከተማ ውስጥ የሚገኝ ታላቅ እና ታሪካዊ መስጅድ ነው።
ትርጉሙም “የነቢዩ መስጅድ” ማለት ሲኾን የቅድስና ደረጃውም መካ ከሚገኘው ከታላቁ አል-መስጅድ አል-ሐራም ቀጥሎ ይጠቀሳል።
የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መቃብር የሚገኘውም በዚሁ ስፍራ ነው። ይህ ቦታ የተከበረው ጄነት ወይም የነቢዩ ክፍል በመባል ይታወቃል።
ዛሬ በሳይቴክ ዘመንኛ ልንዳስስ የወደድነው በታላቁ አል-መስጂድ አን-ነበዊ ውስጥ ያሉትን ድንቅ የቴክኖሎጂ ገጽታዎች ነው። መስጅዱ በርከት ያሉ የቴክኖሎጂ ገጽታን የተላበሰ ነው።
ቴክኖሎጅዎቹ በዋናነት የአካባቢውን የሙቀት ሁኔታ ለማስተካከል እና አማኙ የአምልኮ ተግባሩን በጥሩ ኹኔታ እንዲፈጽም የሚረዱ ናቸው።
ከእነዚህ መካከል ተንቀሳቃሽ ጉልላቶች ተጠቃሾች ናቸው። በመስጅዱ ጣራ ላይ 27 ግዙፍ ጉልላቶች ይገኛሉ። ጉልላቶቹ እንደ አየር ሁኔታው እና እንደአስፈላጊነቱ የሚከፈቱ እና የሚዘጉ ናቸው።
እነዚህ ጉልላቶች ቦታው እንዲቀዘቅዝ እና አየር እንዲያገኝ ተብለው የተሠሩ ናቸው። በግቢው ውስጥ የተተከሉ 250 የሚደርሱ አውቶማቲክ ጃንጥላዎች ይገኛሉ።
ቀን ቀን የፀሐይ ሙቀትን ለመከላከል የሚዘረጉ እና ማታ ማታ ደግሞ ተመልሰው የሚታጠፉ ናቸው። ጥላዎቹ የሚቆሙባቸው ምሰሶዎች ውስጣቸው ውኃ የተሞላ የማቀዝቀዣ ሥርዓት አላቸው።
ከላይ የፀሐይ ሙቀትን በመከላል ብቻ አይደለም አካባቢውን ቀዝቀዝ ለማድረግ የሚያስችሉት ነገር ግን ከመሬት በታች በተገጠመ ዘመናዊ የአየር ማቀዝቀዣ ሥርዓትም ጭምር በመታገዝ ነው።
ለሰላት እና ለአዛን ማድረሻ የሚጠቀሙት የድምጽ ሥርዓት ዘመናዊ በመኾኑ በታለምዶ የገደል ማሚቶ ብለን የምንጠራው (ኢኮ) ሳይፈጥር በጥራት ማድረስ ያስችላል።
መስጅዱን በአካል መጎብኘት ለማይችሉ አማኞች የቨርችዋል ሪያሊቲ ቱር ወይም ምናባዊ ጉብኝት የሚያደርጉበት ቴክኖሎጂም ተሠርቶለታል።
በዚህ ቴክኖሎጂ በመታገዝ አማኞች መስጅዱን ከየትኛውም የዓለም ክፍል ኾነው በምናብ እንዲጎበኙ ይረዳል።
በጣም ብዙ ሰው በሚኖርበት ጊዜ የሕዝቡን ጥግግት ከኮምፒውተር ሥርዓት ጋር በተሳሰሩ ካሜራዎች መጠቆም የሚያስችል መተግበሪያም አለው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበክልሉ ያለውን የመሬት ሃብት በአግባቡ በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አስታወቀ።
Next article“ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በተግባር ስለኖራችሁ እናመሰግናለን” ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ