
ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀሙን እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ “በክልሉ ያለውን የመሬት ሃብት በአግባቡ በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል።
ቢሮው በተዋረድ ካሉ የተቋሙ አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በ2017 በጀት ዓመት አመርቂ ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል።
የይዞታ ማረጋገጫ መስጠት፣ የልማት ተነሽ አርሶ አደሮችን ካሳ የማስከፈል እና የማቋቋም ሥራዎችን ጨምሮ የገጠር መሬት አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል ረገድ አበረታች ውጤቶች ታይተዋልም ነው ያሉት።
በጀት ዓመቱ በብዙ ፈተናዎች ያለፈ ቢኾንም የክልሉን የመሬት ሃብት ለማልማት የነበረው ርብርብ ከፍተኛ እንደነበር በመድረኩ ላይ ተነስቷል።
የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀምን ለማሻሻል ታሳቢ ተደርገው የወጡ መመሪያዎችን ሳይሸራረፉ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል።
በአማራ ክልል የተቀረፀውን የልማት እና አሻጋሪ እቅድ ታሳቢ ባደረገ መንገድ የክልሉ መሬት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ማዘጋጀቱን ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። በእቅዱ ላይም የጋራ መግባባት በመፍጠር ተግባራዊ ለማድረግ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።
ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀሙን እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረኩን ሲያካሂድ የመሬት ቢሮ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ የዞን እና የወረዳ የመሬት ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ:- ኤልያስ ፈጠነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን