
ደሴ፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጡሩሲና መስጅድ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከከሚሴ ከተማ በ16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በደዋ ጨፋ ወረዳ ሃሮ ባቄሎ ቀበሌ ይገኛል።
ጥሩሲና መስጅድ የተሠራበት ቦታ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ነበር። “የነብር ተራራ” ተብሎ ይጠራ እንደነበርም ይገለጻል።
መስጅዱን የገነቡት ሼህ ሙሐመድ አማን ቦታውን ከተመለከቱት በኋላ “ጥሩሲና” ብለው ሰየሙት። ትርጓሜውም “ጥሩ፣ ንፁህ ቦታ” እንደማለት ነው።
ከዛም በስፍራው ልዩ ሀገር በቀል ኪነ ሕንፃዊ ጥበብ የታየበት ግዙፍ መስጅድ መሥራት ተጀመረ። ለአምስት ዓመታት መስጅዱ ሲታነጽ ቆይቶም በ1977 ዓ.ም ተመርቋል።
የጡሩሲና መስጅድ ለአማኙ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ እስከ 2009 ዓ.ም ከቆየ በኋላ መስጅዱ በደረሰበት ተፈጥሯዊ አደጋ ውድመት ደርሶበትም ነበር።
የመጀመሪያው የጡሩሲና መስጅድ በባሕላዊ መንገድ በሣር እና በግዙፍ እንጨቶች የተሠራ ነበር፡፡
ከቆይታ በኋላ ይህንን ታሪካዊ እና ጥንታዊ መስጅድ ዳግም ለመሥራት ርብርብ ተደርጎ ወደ ሥራ ተገባ።
የመጀመሪያ ፈተና የነበረው መስጅዱ የሚገነባበትን በርከት ያለ የአበሻ ጽድ ማግኘት ነበር። ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ ዳግም ለመገንባት የአበሻ ጽዱ እጅግ አስፈላጊ ነበር።
የአበሻ ጽድን ከመጥፋት ለመከላከል መቁረጥ ተከልክሎ የነበረ ቢኾንም ለመስጅዱ ግንባታ በክልሉ ምክር ቤት ተወስኖ ፍቃድ ተሰጠ።
እጅግ ግዙፍ የኾኑትን የአበሻ ጽድ እንጨቶችን ለመቁረጥ፣ ለማጓጓዝ እና ለማቆም ብዙ ጉልበት እና ጊዜንም ወስዷል። በዚህም አጠቃላይ የመስጅዱ መልሶ ግንባታ ስምንት ዓመታትን ሊወስድ ችሏል።
የመስጅዱ ጣሪያ ከሳር ወደ ቆርቆሮ ከመቀየሩ ውጭ መስጅዱ ሲገነባ የቀድሞ ማንነቱን በጠበቀ መልኩ መኾኑ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ይዘቱ እንደተጠበቀ እንዲኾን አስችሎታል።
መስጅዱ በሕዝብ መዋጮ እና በክልሉ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ዳግም አምሮ እና ተውቦ እውን ሊኾን ችሏል።
በግንባታው ሂደትም በርካታ የሰው ቁጥር እንደተሳተፈበት ይነገራል።
ሴት እና ወንድ የሃይማኖቱ ተከታዮች ለየብቻ በጾም፣ በዱዓ እና በሃይማኖታዊ ትምህርት መንፈሳዊ ሕይዎትን እየመሩ ይኖሩበታል።
የጡርሲና መስጅድ በወረዳው አንዱ የቱሪዝም መዳረሻ ነው።
ብዙዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመምጣት የመውሊድ በዓልን በጡሩሲና መስጅድ በድምቀት ያከብራሉ።
ዘጋቢ:- መስዑድ ጀማል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን