
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 500ኛው የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓል በአዲስ አበባ አነዋር መስጅድ እየተከበረ ነው።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ ፈትሁዲን ሐጂ ዘይኑ አሏህ በቁራኑ ላይ የእዝነት ነብይ ብሎ የጠቀሳቸው ነብይ ናቸው ብለዋል።
“ወደ ቀጥተኛው መንገድ የሚመራ ነብይ ተብለው በቁራን የተጠቀሱት ነብይ ባህሪ ለእኛም አንዲሰጠን መውሊዱን ስናከብር ዱአ እናደርጋለን” ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳን ሼህ አብዱልከሪም በድረዲን መውሊድ የኢትዮጵያ እሴት እንደኾነ ተናግረዋል።
መውሊድ የመቻቻል እና የመረዳዳት ምልክት እንደኾነም ነው የጠቆሙት። በዓሉ ትላንትም ሲከበር ቆይቷል ነገም ይከበራል ነው ያሉት።
መውሊድ በዚህ ቀን ለነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያለን ደስታ እና ፍቅር የሚገለጽበት እንደኾነም ጠቁመዋል።
ይህ ደግሞ በእስልምና አስፈላጊው ነገር ነው ብለዋል።
በፆም፣ የተቸገሩትን በማብላት እና በተለያየ መንገድ ማክበር ይቻላል ያሉት ሼህ አብዱልከሪም ዋናው ጉዳይ ለነብዩ ፍቅር መግለጹ እንደኾነ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን