የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል ላይ ትኩረት እንደሚደረግ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት አስታውቋል።

3
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸሙ እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅዱ ላይ ከዞን መምሪያ እና ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
‎ውይይቱን የከፈቱት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) ቢሯቸው በ2017 በጀት ዓመት የንግድ ሥርዓቱን በማሳለጥ ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መሥራቱን ገልጸዋል።
‎በፌዴራል ደረጃ በተደረገ ውድድርም ቢሮው በሁለት ዘርፎች ሁለተኛ ደረጃ ማግኘቱን ጠቅሰዋል።
የጥራጥሬ እና ቅባት እህል ኤክስፖርት ላይም የተሸለሙ ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ለውጤቱ የቢሮው የተዋረድ ተቋማት ድጋፍ እና ጥረት ከፍ ያለ መኾኑን አንስተዋል።
‎የ2017 በጀት ዓመትን ጅማሮዎች እና ስኬቶች በማጠናከር ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል እና የግብይት ሠንሰለትን ማሳለጥን ጨምሮ በትኩረት የሚፈጸሙ ሥራዎች እንዳሉም ተናግረዋል።
‎ሕገ ወጥ ደላላን፣ አላስፈላጊ ኬላን እና ሕገ ወጥ ንግድን ‎መከላከል በ2018 በጀት ዓመት ትኩረት የሚሰጣቸው መኾኑን ዶክተር ኢብራሂም አጽዕኖት ሰጥተዋል።
‎የውጭ ምንዛሪ ግኝትን የማጠናከር ጉዳይም ትልቁ አደራ እና ኀላፊነት መኾኑንም አንስተዋል።
‎ከኋላ ቀር እና ውድድር ከጎደለው የንግድ ሥርዓት መውጣት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
‎ጅምሮችን እና ምቹ ኹኔታዎችን በመጠቀም የበለጠ መሥራት እና የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን ስኬታማ መኾን ይጠበቃል ነው ያሉት። በዚህም ሕዝቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ዶክተር ኢብራሂም አስረድተዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅዱ የወጣቶች ነው።
Next article“መውሊድ ለነብዩ ሙሐመድ ያለን ፍቅር የሚገለጽበት ነው” እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።