የ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅዱ የወጣቶች ነው።

2
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የዓለም ወጣቶች ቀን የማጠቃለያ ዝግጅት እየተካሄደ ነው።
ዝግጅቱ “የተደመረ የወጣቶች አቅም ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በክልላዊ የማጠቃለያ ዝግጅቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ሲከበር ሁለት ወሳኝ ዓላማዎችን ይዞ መኾኑን ገልጸዋል።
ዓለም ወደ አንድ መንደር እየመጣች መኾኗ እና ከዓለም ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር የወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ ደርሻ ያለው በመኾኑ ያን አቅም ለመጠቀም ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም የወጣቶች ሀገር መኾኗን ተናግረዋል። ዓለም አቀፍ የወጣቶችን ቀን ስናከበር የተደመረ የወጣቶችን አቅምን ለዘላቂ ልማት ግቦች ለመጠቀም ነው ብለዋል።
የአንዲት ሀገር የመልማት እና ያለ መልማት ጉዳይ የሚመዘነው በወጣቶች አቅም መኾኑንም ተናግረዋል።
በሀገር ላይ የወጣቶች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማደግ እንደሚገባውም ገልጸዋል። ወጣቶች በግጭት አፈታት ዙሪያ ያላቸውን ሚና ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የመጀመሪያው አማራጭ ሰላማዊ አማራጭ ነው ያሉት ኀላፊው ወጣቶች ደግሞ ለሰላም ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ወጣቶች ወደ ግጭት ባለመግባት፣ ግጭትን በማረገብ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ አለባቸው ነው ያሉት።
የአማራ ክልል የ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ የወጣቶች ነው ያሉት ኀላፊው በአሻጋሪ እድገት እና በዘላቂ ልማት ዕቅዱ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ አስገንዝበዋል።
ዕቅዱ የወጣቶችን አቅም እንደሚፈልግም ተናግረዋል። ዕቅዱ የትውልድ በመኾኑ የሚፈጸመው በወጣቶች ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት መኾኑንም ነው ያነሱት።
በዘላቂ የግጭት አፈታት ላይም የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው ነው ያሉት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመኾን ራሳቸውን በቴክኖሎጂ እንዲያበቁም አሳስበዋል።
ራሱን በቴክኖሎጂ ያበቃ ብቁ ትውልድ ሀገርን ተወዳዳሪ እንደሚያደርግም አመላክተዋል።
ጊዜው የክልሉ የመነሳት እና የማንሰራራት ነው ያሉት ኀላፊው ወጣቶች ለክልሉ ማንሠራራት ዘመን የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“እቅዳችን ለማሳካት እንደ አንድ ልብ አሳቢ እና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በጋራ ልንቆም ይገባል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)
Next articleየንግድ ሥርዓቱን በማዘመን ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል ላይ ትኩረት እንደሚደረግ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት አስታውቋል።