በ2018 የትምህርት ዘመን ያለፈውን የትምህርት ክፍተት ለማካካስ በትኩረት ይሠራል።

2
ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኀበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት ነባራዊ ኹኔታ በአካዳሚክ ዘርፍ የብዙ ዓመታትን የትውልድ ክፍተት የሚፈጥር በመኾኑ ይህንን ለመቀየር የኹሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
የ2018 የትምህርት ዘመን ባለፉት ዓመታት ያጋጠመውን የትምህርት ክፍተት ለማካካስ ርብርብ የሚደረግበት መኾኑንም አንስተዋል።
ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ባለፉት ሁለት ዓመታት ያልተመዘገቡትን እና በዚህ ዓመት መመዝገብ የሚገባቸውን ተማሪዎች ጨምሮ እንዲመዘገቡ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ከመደበኛ የትምህርት ተግባራት በተጨማሪ በተመሣሣይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያለፋቸውን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችንም ለማስቀጠል አማራጮችን ኹሉ እንጠቀማለን ነው ያሉት።
የ2018 በጀት ዓመት የትምህርት ዘመን የ25 ዓመት አሻጋሪ እቅድና የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ የመጀመሪያ መሠረት የሚጣልበት በመኾኑ በተለየ ትኩረት የሚሠራበት ስለመኾኑም ነው ዶክተር ሙሉነሽ ያነሱት።
በበጀት ዓመቱ የፈተና እና ምዘና ሥርዓትን የሚያሳልጡ ሲስተሞችንና ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ተቋሙን የማዘመን ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ማኀበረሠቡ ለትምህርት የሚሰጠው ትኩረትና ግንዛቤ እንዲጨምር ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ልጆች በትምህርት አልፈው ከቴክኖሎጅ ጋር ተላምደውና ክህሎት አግኝተው ሥራ ፈጣሪ እንዲኾኑ ወላጆችም ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
በውይይቱ የዞኖችና ከተማ አሥተዳደር የትምህርት መምሪያ ኀላፊዎች እየተሳተፉ ሲኾን የንቅናቄ መድረኩ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየጀነት ሴት-እሙ አይመን
Next article“እቅዳችን ለማሳካት እንደ አንድ ልብ አሳቢ እና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በጋራ ልንቆም ይገባል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)