የጀነት ሴት-እሙ አይመን

5
ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 500ኛው የመውሊድ በዓል በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ነው። በዓሉን ምክንያት አድርገንም ስለአንዲት ጽኑ፣ ታታሪ እና ታማኝ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አሳዳጊ ልናስቃኛችሁ ወደድን።
የዘር ሀረጓ በዘመኑ ስደት እና ባርነት ከሀገራቸው ገፍቶ ካስወጣቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል ይመዘዛል፡፡
እንዴት እና በምን ሁኔታ ለአስከፊው የባርነት ሕይዎት እንደተጋለጠች በውል ባይታዎቅም በዚያ የጨለማ ሕይዎት ውስጥ አልፋ ለብዙዎች ብርሃን የፈነጠቀች ጽኑ፣ ታማኝ፣ ተወዳጅ እና የጀነት ሴት እንደነበረች ግን የሕይዎት ታሪኳ ያስረዳል፡፡
መካ የእስልምና ሃይማኖትን ስትከለክል እና የእምነቱ ተከታዮች ሲሳደዱ ሁለት ጊዜ ሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ከተሰደዱት መካከል ይህች ሴት ትገኛለች፡፡
ከሀገሯ በባርነት የወጣች፣ ስለሃይማኖቷ ደግሞ ወደ ሀገሯ መልሳ እና መላልሳ የተሳደደች ጽኑ እና ብርቱ እናት ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡
እንደ ቢላልም እንደ አልነጃሽም ኢትዮጵያን እና እስልምናን በጽኑ መሠረት ካቆራኙት ብርቱ እና ጽኑ ሰዎች መካከል ይህች ሴት ተጠቃሽ ናት፡፡
ቤተሰቦቿ ያወጡላት እና የልጅነት መጠሪያ ስሟ “በረካ አል ሐበሽ” ይባላል፡፡ “እሙ አይመን” ወይም “የአይመን እናት” የሚለው ስሟ ደግሞ እንደ አረቦቹ ባሕል በመጀመሪያ ልጇ ስትጠራ ነው፡፡
እሙ አይመን በረካ ወይም የአይመን እናት የአሏህን መልዕክተኛ በእምነት ተቀብላ በጽናት ያሳደገች የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሁለተኛ እናት ናት፡፡ ለነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልጅነት ዘመናቸው ሞግዚት እና የወጣትነት ዘመናቸው እህት ናት፡፡
እሙ አይመን ሃይማኖቷን አጥባቂ እና ነብዩን ጠባቂ በመኾኗ በብዙዎች ዘንድ አብዝታ ትወደድ ነበር ይባላል፡፡
እሙ አይመን በረካ ከብዙ ሴቶች በብዙው ትለያለች ያሉን የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ መምህር የኾኑት ሼክ ሀሰን ገላው ናቸው፡፡ መምህሩ እሙ አይመንን ሲገልጿትም ይህች ሴት ከብዙዎች መካከል ተለይታ በመከራ የጸናች፣ በቃሏ የተገኘች፣ በአሏህ ፍቅር የተገራች እና ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር እስከ ሕይዎት ዘመን ፍጻሜ ከጎናቸው ያልተለየች ሴት ነች፡፡
ይህች ሴት በአሏህ መልዕክተኛ “የጀነት ሴት” ተብላ የተጠራች ብርቱ እና ታታሪ ሴት ነች፡፡ ይህች ሴት በምድር የተቀበለችውን አደራ በሰማይ የመለሰች፤ ላመነችበት እውነት ሞትን ሳትፈራ እና ለራሷ ሳትራራ በመከራ መካከል ደጋግማ የተመላለሰች ብርቱ ሴት ነበረች ይላሉ፡፡
እሙ አይመን በረካ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወላጅ እናት አሚናን በመከራዋ ዘመን ከጎኗ ኾና ያበረታች፣ በእርግዝናዋ ወቅት ለአፍታ ሳትለይ የተንከባከበች፣ ስትወልድ በቅርብ የተገኘች እና ያረሰች እድለኛ ኢትዮጵያዊት ሴት ናት ይላሉ መምህሩ፡፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ይህችን ምድር ሲቀላቀሉ በቅድሚያ ያረፉት በእሙ አይመን ክንድ ላይ ነበር፡፡ የነብዩን እናት አሚናን ብቻዋን አልቅሳ የቀበረች፤ ልጇን ነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ተቀብላ ያሳደገች እና በ63 ዓመታቸው በሞት ሲለዩ አምርራ ያዘነች የመከራ ዘመን ጽናት፤ የፈተና ዘመን ብርታት ተምሳሌት ተደርጋ ትወሰዳለች ይሏታል፡፡
የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ “አብዛሃኛውን ጊዜም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከበረካ አንገት አካባቢ እጃቸውን ተደግፈው ይተኙ ነበር” ይላሉ፡፡
ሼክ ሀሰን እንደሚሉት ነብያችን ከልጅነት እስከ እውቀት፤ ከልደት እስከ ሞት ድረስ ከሚያውቋቸው እና ከጎናቸው ካልተለዩ ሶኻባያዎቻቸው መካከል እሙ አይመን አንዷ ናት፡፡ ለዚያም ይመስላል ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በአንደበታቸው “እሙ አይመን ከእናቴ በኋላ እናቴ ነሽ” ሲሉ የመሰከሩላቸው፡፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በአንደበታቸው “የጀነት ሴት” ያሏትን እሙ አይመንን አብዝተው ከመውደዳቸው የተነሳ ከሶኻባዎቻቸው መካከል በጣም ለሚወዱት እና በስማቸው እስከመጠራት ለደረሰው ዘይድ ኢብን አልሐሪሳ ድረዋታል፡፡
ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች እሙ አይመንን እንደ አንድ የእስልምና ሃይማኖት ባለውለታ ስናያት ኢትዮጵያዊ በመኾኗ ብቻ አይደለም የሚሉት ሼክ ሀሰን የእስልምና ሃይማኖት በፈተና፣ በመሳደድ እና በችግር ላይ በነበረበት ወቅት ለቃሏ እና ለሃይማኖቷ ጹኑ ኾና በመገኘቷ ነበር ይላሉ፡፡
ዛሬም ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ለሃይማኖት መጽናትን፣ ለሀገር መበርታትን፣ ለቃል መገኘትን እና ላመኑበት መሞትን ከእሙ አይመን ሊማሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleመውሊድ እና ጀማ ንጉስ!
Next articleበ2018 የትምህርት ዘመን ያለፈውን የትምህርት ክፍተት ለማካካስ በትኩረት ይሠራል።